ኢትዮጵያ ቡና ክሪዚስቶም ንታምቢ ደሞዙን እንዲመልስ ወሰነ

ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ ወር ከጅማ አባ ቡና ጋር ተለያይቶ ክለቡን በተቀላቀለው ዩጋንዳዊው አማካይ ክሪዚስቶም ንታምቢ ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል፡፡ ቡናማዎቹ አማካዩ እስካሁን የተከፈለውን ደሞዝ እንዲመልስም እሁድ ታህሳስ 29 በተፃፈ ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡

ንታምቢ በጅማ አባ ቡና ያሳየውን ድንቅ አቋም ተከትሎ ለቡና ቢፈርምም በአመዛኙ የሊግ ጨዋታዎች ላይ መጫወት አልቻለም፡፡ ተጫዋቹ በጉዳት ሳቢያ ከሜዳ እንደራቀ ቢነገርም ክለቡ ግን ጉዳት ሳያጋጥመው አታሎኛል ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል ይህ ተጫዎች ውድድሩ ከጀመረ አስር ጨዋታዎች መካከል መሰለፍ የቻለው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሲሆን በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ጉዳት ላይ እንደሆነ በተደጋጋሚ በመግለጽ እና የሀኪም ማስረጃዎች በማቅረብ ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ያሳሰበው ክለባችን ባደረገው የ ኤም አር አይ ምርመራ ተጨዋቹ ምንም አይነት ጉዳት ያልነበረበትና የሌለበት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም በዛሬው እለት ለተጫዎቹ ክለባችን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የሰጠ ሲሆን በደብዳቤው ላይም ያደረገውን ስህተት በዝርዝር በመግለጽ ያልሰራበትን ገንዘብ እንዲመልስ ተጠይቋል፡፡

በዩጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ክለቦች የእግርኳስ ህይወቱን የመራው ንታምቢ አነጋጋሪ ጉዳይ ውስጥ ሲዘፈቅ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ አይደለም፡፡ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከጅማ አባ ቡና ጋር ከተለያየ በኃላ ለሁለት ክለቦች ፊርማውን አኑሯል በሚል አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተጫዋቹ ተገቢነት ዙሪያ እስከፌድሬሽኑ ድረስ ለውሳኔ እንደሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *