ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለጎል አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡

ባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች ሳምንት ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና ከተሸነፉበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት አስተናግዶ የነበረውን አዲስአለም ተስፋዬን በኄኖክ ድልቢ የተኩ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ አሰልጣኛቸው አሸናፊ በቀለ እየተመሩ ጨዋታዉን ያደረጉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ከአዳማ ከተማው ሽንፈት የሶስት ተጨዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። በዚህም ሱሌማና አቡ ፣ ዳንኤል ራህመቶ እና ጫላ ድሪባ በዮሀንስ በዛብህ ፣ ተስፋዬ መላኩ እና ሲሴይ ሀሰን ተተክተዋል።

በፌዴራል ዳኛ ሐብታሙ መንግሰቴ አብሳሪነት በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ሙሉ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ የበላይነት የነበረው ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ የጠራ የጎል ማስቆጠር ዕድል መፍጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡

ጨዋታው እንደተጀመረ ኤሌክትሪኮች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለማምራት ሲሞክሩ መሀል ላይ የተቆረጠችው ኳስ ዮሀንስ ሱጌቦ እግር ስር ገብታ ከግራ መስመር ሲያሻገራት ዳዊት ፍቃዱ ማስቆጠር ባይችልም የጨዋታው የመጀመርያ የግብ ዕድል ሆና ተመዝግባለች። ወደ ግራ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ የበላይነት መውሰድ የቻሉት ሀዋሳዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አቅጣጫ ደስታ ዮሀንስ ያሻገራትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ባልተረጋጋ አቋቋም ውስጥ ወደ ግብ መትቶ በግቡ አናት ሲወጣበት እና በሁለት አጋጣሚዎች ደስታ ዮሀንስ እና ታፈሰ ሰለሞን ያደረጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ዮሀንስ በዛብህ  አማካይነት ከሽፈዋል፡፡ በተጨማሪም በ40ኛው ደቂቃ ሙሉአለም ረጋሳ በረዥሙ ባሻገረው ኳስ ዳዊት ፍቃዱን ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ አገናኝቶት የነበረ ቢሆንም ዳዊት አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ዮሃንስ ደርሶ ያዳነበት ሙከራም ሀዋሳ ከተማ ለነበረው የበላይነት ሌላኛው ማሳያ ነበር፡፡

ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ እና በርካታ ካርዶች በታዩበት በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌትሪኮች ተሻሽለው ቢቀርቡም ሀዋሳ ከተማ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የእንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራ የበላይነት ነበረው፡፡ በ46ኛው ደቂቃ ከሙሉአለም የተሸገረውን ኳስ ጋብሬል በግንባሩ ሲገጭ ኳስ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚ የሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር፡፡ 54ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ደስታ ዮሀንስ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የመታትን ኳስ በዕለቱ ድንቅ የነበረው ዮሀንስ በዛብህ ሲመልሳት ያቡን ዊሊያም አግኝቶ በድጋሜ ቢሞክርም አሁንም ኳስ ዮሀንስን ማለፍ ሳትችል ቀርታለች። 55ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ እየገፋ ሲገባ በተስፋዬ መላኩ ተጠልፌያለሁ ብሎ የወደቀው ፍሬው ሰለሞን የፍፁም ቅጣት ምት ይገባኛል በሚል ውዝግብ ሲፈጥር ዳኛው ሰድቦልኛ በማለት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል፡፡

ከፍሬው መውጣት በኃላ የሀዋሳ ከተማ በጎዶሎ ተጫዋቾች መጫወትን በመጠቀም ኤሌትሪኮች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ 60ኛ ደቂቃ ላይ አል ሀሰን ካሉሻ ከዲዲዬ ለብሪ የተሸገረለት እና ያመከነው ኳስም በጠረ የግብ ዕድልነት የሚጠቀስ ነበር፡፡ቀስ በቀስ የበላይነታቸውን ማስመለስ በቻሉት ሀዋሳዎች በኩል 70ኛው ደቂቃ ላይ በደስታ ዮሀንስ ፣ 77ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ ድልቢ እንዲሁም 79ኛው ደቂቃ ላይ በሲላ መሀመድ አማካኝነት የሞከሯቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ረጅም ደቂቃዎች የፈጀ ተቃውሞ በዕለቱ ዳኛ ላይ ያሰሙ ሲሆን ሀዋሳዎችም በአምበሉ ደስታ ዮሀንስ አማካኝነት ፍሬው ያገኘው ቀይ ካርድ ተገቢ አይደለም እንዲሁም ፍፁም ቅጣት ምትም ተከልክለናል በማለት ክስ አስይዘዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ ሀዋሳ ከተማ

“በኛ በኩል ጥሩ ውጤት ማለት ማሸነፍ ነው፡፡ ያ አልሆነም። ዛሬ ሶስት ነጥብ አላገኘንም፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ጥሩ ነው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት በእንቅስቃሴ ጥሩ እየሆንን ነው። የመጨረሻ ግብ ማስቆጠር ላይ ግን ክፍተቶች አሁንም አሉብን፡፡ በተረፈ በእግር ኳስ ሁሉም ነገር ያጋጥማል፡፡ የተለየ ችግር በቡድኔ ላይ የለም፡፡ ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች  የመቐለው  ብቻ ጥሩ ያልነበርንበት ነበር፡፡ ከዛ ውጭ ግን ጎል አለማስቆጠራችን ለውጤት ከመጓጓት አንፃር ነው፡፡ በቶሎ ከዚህ ወጥተንም እንሻሻላለን ብዬም እገምታለሁ፡፡”

ቅጣው ሙሉ – ኤሌክትሪክ (የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ)

” ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ መልካም አጋጣሚም ፈጥረን ነበር፡፡ ማንኛውም ቡድን ሲመጣ ለማሸነፍ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ ካልተቻለ ደግሞ አቻ፡፡ እኛም ያን ነበር ይዘን የመጣነው፡፡ የተጎዱ እና የተቀጡ ተጨዋቾች ሲመለሱ ቡድናችን ከዚህ አስከፊ የውጤት ቀውስ መውጣቱ አይቀርም”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *