​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | አአ ከተማ ነጥብ ሲጥል ሰበታ እና ኢኮስኮ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 9ኛ ሳምንት 4 ጨዋታዎች እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እሁድ ተደርገው ኢኮስኮ እና ሰበታ ሲያሸንፉ መሪው አአ ከተማ ነጥብ ጥሏል።

በያያ ቪሌጅ 7፡00 ሰዓት ላይ ኢኮስኮን ከ ለገጣፎ ለገዳዲ ያገናኘው ጨዋታ በኢኮስኮ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ33ኛው ደቂቃ ላይ በክሪ መሐመድ ያሻማውን የማዕዘን ምት የለገጣፎ ተከላካዮች ኳሱን በአግባቡ ከግብ ክልላቸው ሳያርቋት በመቅረታቸው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አክርሮ በመምታት ኢኮስኮን ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ ያመዘነበት እና እምብዛም የጎል ሙከራ ያልታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በኢኮስኮ 1-0 መሪነት ተገባዷል።

የኢኮስኮን ጎሎች ያስቆጠሩት ሙሉጌታ እና አሳምነው

ከዕረፍት መልስ  ተጭነው መጫወት የቻሉት ለገጣፎዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቢደርሱም ከዕረፍት መልስ የኃላ ክፍሉን ያጠናከረው የደግአረገን ቡድን ማስከፈት ሳይችል ቀርቷል። ይልቁንም በ67ኛው ደቂቃ በረጅሙ ወደ አደጋ ክልል የተላከችውን ኳስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በድጋሚ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ በመምታት ወደ ግብነት ለውጦ የኢኮስኮን መሪነት አስፍቷል። በ87ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አሳምነው አንጀሎ የማሳረጊያዋን ጎል በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ጨዋታው በኢኮስኮ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ቀጥሎ በያያ ቪሌጅ በ9፡00 ላይ የተካሄደው የሱልልታ ከተማ እና ፌዴራል ፖሊስ ጨዋታ ያለጎል በአቻ ውጤት ተፈፅሟል። ሁለቱም ቡድኖች በርካታ የግብ እድሎች በፈጠሩበት ጨዋታ አብነት ደምሴ ፣ሊቁ አልታየ እና አብዱራሂም ዘይን ጥሩ የጎል ሙከራዎችን ሲያደርጉ በሱልልታ ከተማ ቶሎሳ ንጉሴ ፣ ጥላሁን ጌታቸው ፣ አብዱልቀድር ቀድሮ እና ቢንያም አማረ ያደረጉት ሙከራ ወደ ግብነት ሳይለወጥ ቀርቷል፡፡

ሰበታ ከተማ ከተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል በማስመዝገብ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል። ሰበታ ላይ በተካሄደው ጨዋታ ሰበታ ከተማ ኄኖክ መሀሪ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል ወሎ ኮምቦልቻን 1-0 አሸንፏል።

አዲስ አበባ ከተማ በሜዳው ነጥብ በመጣል ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት አጥብቧል። መድን ሜዳ ላይ አክሱም ከተማን ያስተናገደው አአ ከተማ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ እያስቆጠረ ያለው ፍቃዱ ዓለሙ ከመረብ ባሳረፈው ኳስ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ሙሉጌታ ሽኩር አክሱምን አቻ አድርጎ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል። አዲስ አበባ ከተማዎች በዕለቱ ዳኝነት እና ውሳኔ አሰጣጥ ቅር መሰኘታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

በ 8ኛው መርሃ ግብር ይካሄዳል ተብሎ ታስቦ የነበረው የነቀምት ከተማ እና የየካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በዚህ ሳምንት ነቀምት ላይ ተካሂዶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

በዚህ ምድብ በ9ኛ ሳምንት ሊካሄዱ የነበሩ 4 ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ሲሆን ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ መድን እና ከ

የቡራዩ ከተማ ጨዋታ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ መድንን ከውድድር በማገዱ መካሄድ ያልቻለ ጨዋታ ነው። መድን ከአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጋር በተያያዘ የተወሰኑት ውሳኔዎች ተግባራዊ እስኪደረጉ ድረስ ማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ በመወሰኑ ነው መድን ይህ ሳምንት ጨዋታ ያለፈው።

የካ ክፍለ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ ፣ አውስኮድ ከ ነቀምት ከተማ እንዲሁም ሽረ እንዳስላሴ ከ ደሴ ከተማ ሌሎች በዚህ ሳምንት ያልተካሄዱ መርሀ ግብሮች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *