​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | መሪው ዲላ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

ቅዳሜ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በተጀመረውና እሁድ በቀጠለው  የምድብ ለ 9ኛ ሳምንት ዲላ ከተማ ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ጅማ አባ ቡና እና ደቡብ ፖሊስም አሸንፈዋል።

ባለፈው ሳምንት ከሀላባ ጋር ባደረገው ጨዋታ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ከከተማው 150 ኪሎሜትር ርቀት እንዲጫወት የተወሰነበት ሀምበሪቾ ቅዳሜ ወደ ድሬዳዋ አምርቶ ከናሽናል ሴሜንት ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-1 አሸንፏል። ናሽናሎች በ66ኛው ደቂቃ ላይ በቢንያም ጥዑመልሳን ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም አልዓዛር አድማሱ በ72ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ፍፁም ደስ ይበለው አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሀምበሪቾዎች አሸንፈው ወጥተዋል።

ቅዳሜ የተካሄደው ሌላው ጨዋታ በጅማ አባቡና እና ነገሌ ከተማ መካከል የተደረገው ነው። ቴዎድሮስ ታደሰ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጎል ባለሜዳዎቹ አባ ቡናዎችን ሙሉ ሶስት ነጥብ አስጨብጧል። በጨዋታው የአባ ቡና ደጋፊዎች አሰልጣኝ ግርማ ሀ/ዮሀንስ ላይ ተቃዋሞዎችን ሲያሰሙ ተስተውሏል፡፡

ወደ ሆሳዕና ያመራው ደቡብ ፖሊስ ዋና አሰልጣኙ እዮብ ማለን ለአርባምንጭ ከተማ አሳልፎ የሰጠው ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 አሸንፎ ተመልሷል።  ደቡብ ፖሊሶች 10ኛው ደቂቃ በኃይሉ ወገኔ ባስቆጠረው ግብ መመራት ሲጀምሩ በ35ኛው ደቂቃ ላይ አበባየው ዮሐንስ በቀድሞ ክለቡ ላይ ጎል በማስቆጠር የደቡብ ፖሊስን ግብ ልዩነት ወደ 2 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ከዕረፍት መልስ ሆሳዕናዎች በመለሰ ትዕዛዙ ግብ አማካኝነት ቢያስቆጥሩም ከሽንፈት መዳን አልቻሉም።

ወደ ሚዛን አማን ያመራው ሻሸመኔ ከተማ አሁንም ሽንፈት አስተናግዶ በውጤት ቀውሱ ገፍቶበታል።  ተሸንፎል፡፡ እስከ እረፍት ምንም ግብ ባላስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከዕረፍት መልስ ቤንችማጂ ቡና በጌታሁን ገላው እና ስንታየው አሸብር ግቦች 2-0 በሁነ ውጤት አሸንፏል፡፡

ወራቤ ላይ ካፋ ቡናን ያስተናገደው ስልጤ ወራቤ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን በእጅጉ ማሻሻል ችሏል። በተከታታይ ጨዋታዎች ጎል እያስቆጠረ የሚገኘው ወጣቱ ገብረመስቀል ዱባለ የወራቤን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።

ወደ ድሬዳዋ ያመራው የምድቡ መሪ ዲላ ከተማ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ድሬዳዋ ፖሊስን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል። የዲላን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል በ24ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ማሜጫ አስቆጥሯል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ቡታጅራ ያገናኘው መርሃ ግብር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ወልቂጤ ከተማዋች በ19ኛው ደቂቃ ላይ አትክልት ንጉሴ ባስቆጠረው ግብ መምራት ቢችሉም በ50ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ቶማስ ቡታጅራን አቻ አድርጓል።

ሀላባ ከተማ ዛሬ አዲስ አዳጊው መቂ ከተማን አስተናግዶ 1-1 ተለያይቷል። እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ድረስ ጎል ባልተስተናገደበት ጨዋታ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ሀላባ ከተማ በስንታየው መንግስቱ ጎል አሸናፊ ለመሆን ቢቃረብም በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ከማዕዘን የተሻማችውን ኳስ ዝነኛው ጋዲሳ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመለወጥ መቂ ከተማ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *