​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ – 1ኛ ዲቪዝዮን ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ሲጠናቀቅ ወደ ይርጋለም ያቀናው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲዳማ ቡናን 3-0 አሸንፏል።

በጨዋታው የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም ቀስ በቀስ የበላይ መሆን የቻሉት ንግድ ባንኮች በ20ኛው ደቂቃ ከታሪኳ ደቢሶ የተሻማውን ቅጣት ምት ረሂማ ዘርጋው በግንባሯ በመግጨት ግብ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ሲዳማዎች ከግቧ በኃላ በረድኤት አሳሳኸኝ እና ቱሪስት ለማ አማካኝነት መልካም አጋጣሚን ቢፈጥሩም የአቻነት ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ይልቁኑም በ35ኛው ደቂቃ ዙለይካ ጁሀድ እና ረሂማ ዘርጋው በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሲዳማ የግብ ክልል በመግባት ረሂማ አመቻችታ የሰጠቻትን ኳስ አጥቂዋ አይናለም አሳምነው ወደ ግብነት ለውጣ የንግድ ባንክን መሪነት አስፍታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜም እንደመጀመርያው ሁሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በ60ኛው ደቂቃ በግምት ከ40 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ህይወት ደንጊሶ በቀጥታ በመምታት ወደ ግብነት ለውጣ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ አድርጋለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 በሆነ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከሲዳማ ቡና ጋር በተያያዘ ዜና ዛሬ ክለቡ ባንክን በገጠመበት ጨዋታ አዲስ በተሾሙት ምክትል አሰልጣኝ ደረሰ ዘለቀ እና በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በልጉዳ ዲላ መሪነት ነው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል ያለፉትን ቀናት ከክለቡ ጋር እንዳልነበሩ ታውቋል።

አሰልጣኝ አሰልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል በህመም ምክንያት ባለፉት ቀናት እንዳልነበሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። “ከፍተኛ ህመም ስላጋጠመኝ ከአዳማው ጨዋታ ጀምሮ ህክምና እያደረኩ ያለፉትን ቀናት አልነበርኩም። አሁን ከህመሜ እያገገምኩ ነው። በቀጣይ ቀናት በሙሉ ጤንነት ወደ ክለቡ እመለሳለው። ”

አሰልጣኝ ፍሬው ይህን ይበሉ እንጂ ሶከር ኢትዮጵያ ግን ከክለቡ አካባቢ ባገኘችው መረጃ መሰረት አሰልጣኙ እና ክለቡ ሳይለያዩ እንዳልቀሩ ተሰምቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *