​​የጥር 09 የፕሪምየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሁለተኛ እና አምስተኛ ሳምንት ላይ ሳያስተናግዳቸው በይደር ተይዘው የቆዩ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በጎንደር ይደረጋሉ። ፋሲል ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ወልድያን ከ መቐለ ከተማ የሚያገናኙትን እነዚህን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

ፋሲል ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

(09:00, ፋሲለደስ ስታድየም)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን 2018 ማጣሪያ እየተሳተፈ በነበረበት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራት ተጨዋቾች በላይ በማስመረጡ ይህ ጨዋታ ሳይካሄድ እስካሁን ቆይቷል። አሁን ላይ ቡድኖቹ በሊጉ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ከመቀመጣቸው በተጨማሪም እስካሁን ምንም ሽንፈት አለማስተናገዳቸው የጨዋታውን ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጎታል። በርከት ያሉ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ የቆዩት ሁለቱ ክለቦች ባሳለፍነው ሳምንትም ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ያለ ግብ ነበር የተለያዩት። በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት እና ከመሪው ደደቢት ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት የሚመራውን የዛሬ ጨዋታ ማሸነፍ ለሁለቱም ቡድኖች ግዴታ ይመስላል። አምና በሊጉ አራተኛ ሳምንት ላይ ሲገናኙ የ2-1 አሸናፊ መሆን የቻለው በወቅቱ የሊጉ እንግዳ የነበረው ፋሲል ከተማ ነበር። ዘንድሮስ ታሪክ ራሱን ይደግማል ወይንስ ሻምፒዮኖቹ በመጪው እሁድ የሊጉን መሪ ከመግጠማቸው በፊት በድል ይመለሳሉ የሚሉትን ጥያቄዎች 9፡00 ላይ በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም የሚጅምረው ጨዋታ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።

ፋሲል ከተማ አብዱራሀማን ሙባረክን በቅጣት ሲያጣ ልምምድ የጀመረው ያሬድ ባየህ እና አይናለም ኃይለ ደግሞ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን ይስሀቅ መኩሪያ ግን ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ታደለ መንገሻ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ አሜ መሃመድ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ እና አሉላ ግርማ አሁንም ጉዳት ላይ ሲገኙ ጋዲሳ መብራቴ ከጉዳቱ ቢያገግምም የመሰለፉ ነገር አለየለትም።

ፋሲል ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋነኝነት የ4-3-3 አሰላለፍ ተጠቃሚዎች ናቸው። ሆኖም አተገባበር ላይ ልዩነት ይታይባቸዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ አጨዋወት በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ለማድረግ የሚሞክር በመሆኑ ከበፊቱ በተለየ መሀል ሜዳ ላይ በርከት ያሉ ንክኪዎችን ለማድረግ ይሞክራል። በአንፃሩ ፋሲሎች የመስመር አጥቂዎቻቸውን በፈጣን ቅብብሎች በማግኘት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይታያል። ሁለቱም ቡድኖች እየተከተሉ ያሉት አካሄድ የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ኃላ አስጠግተው ከሚጫወቱ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በቀላሉ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ችግር ላይ እየጣላቸው ቢሆንም እርስ በእርስ በሚያደርጉት የዛሬው ጨዋታ ግን ወደ መሀል ሜዳው ከሚቀርበው የተከላካይ መስመራቸው ጀርባ ክፍተቶች የሚያገኙበት እንደሚሆን ይገመታል። በዚህም እምብዛም በማጥቃት ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሲሆኑ የማይታዩት የቡድኖቹ የመስመር ተከላካዮች ዋነኛ የጥቃት አማራጭ ተደርገው ከሚወሰዱት የተጋጣሚዎቻቸው የመስመር አጥቂዎች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ የሚጠበቅ ይሆናል። በተመሳሳይ እነዚሁ የመስመር አጥቂዎች ከራሳቸው የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸውን ርቀት እያጠበቡ ለአማካይ ክፍላቸው የቁጥር የበላይነትን የማስገኘት ኃላፊነታቸውም የሚፈተሽበት ነው። በዚህ አንፃር ግብ ያስቆጠረ ቡድን ወደ 4-2-3-1 ቅርፅ አድልቶ የሚጫወትበት ዕድል የሰፋ ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ዳዊት እስጢፋኖስ እና አብዱልከሪም ኒኪማን የመሳሰሉት አማካዮች ኳስ የማቀበያ አማራጮቻቸው ከሰፉ ንፁህ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ሌላው የጨዋታው አካል ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የፊት መስመር ተሰላፊዎች በተከላካዮች እና የተከላካይ አማካዮች ላይ ከኳስ ውጪ ሊያሳድሩት የሚችለው ጫና ነው። ሁለቱም ቡድኖች በዚህ አኳኃን ኳስ ከኃላ እንዳይመሰረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሲታሰብ ቀጥተኛ የሆኑ ረዣዥም ኳሶች ወደ ፊት ሊጣሉ የሚችልበት ዕድል እንዲኖር ያደርጋል። በመሆኑም ከላይ የተነሳው አማካይ የኃላ መስመር ክፍል አቋቋም ወደ መሀል መጠጋት ጋር ተዳምሮ የሚፈጠሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሊፈጥር ይችላል። ከነዚህ ነጥቦች አንፃርም ጨዋታው በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ፉክክር የሚስተዋልበት እንደሚሆን ይገመታል።


ወልዲያ ከ መቐለ ከተማ
(11:00, አአ ስታድየም)

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛው ሳምንት በጎ ትዝታን ትቶልን አላለፈም። መላውን የእግር ኳስ ቤተሰብ ድንጋጤ ውስጥ በጣለው አጋጣሚ የደጋፊዎች እግር ኳሳዊ ስነ-ምግባር መልኩን ቀይሮ እና በእጅጉ ከመስመር ወጥቶ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ  እስከማሳጣት የደረሰው ወልዲያ ላይ ሁለቱ ክለቦች ሜዳ ላይ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ነበር። ይህን ተከትሎም ጨዋታው በዕለቱ ሳይካሄድ ቀርቶ በመጨረሻም በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ በመወሰኑ ነው ዛሬ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቀጠሮ የተያዘለት።

ደካማ በሆነ ንፃሬ እስካሁን በሊጉ እኩል ስድስት ግቦችን በተጋጣሚዎቻቸው ላይ ማስቆጠር የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች በመሀላቸው የስድስት ደረጃ ልዩነት እንዲኖር ምክንያት የሆነው የሚያስተናግዱት የግብ መጠን ይመስላል። በዚህም የተሻለ ጥንካሬ ያሳየው መቐለ ከተማ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ወልዲያ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን በሚመራው የዛሬ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለም ከተጋጣሚው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጎ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ማለት የሚችል ሲሆን መቐለዎች ድል ከቀናቸው ደግሞ ራሳቸውን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ማቅረብ የሚችሉ ይሆናል።

የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ የወልዲያው አዳሙ መሐመድ እንዲሁም የመቐለ ከተማው አሌክስ ተሰማ ከጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን ቀድሞ ቅጣት ላይ ከነበሩት ብሩክ ቃልቦሬ እና አማረ በቀለ በተጨማሪ የመቐለው የፊት አጥቂ ጋይሳ ቢስማርክ አፖንግም በአምስት ቢጫ ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

በዚህ ጨዋታ ሜዳ ላይ ሊኖር የሚችለው እንቅስቃሴ የቡድኖቹ የፊት አጥቂዎች ሊያገኙ ከሚችሉት ክፍተት ተነስተን ብንመለከተው ጥሩ ነው። በዚህ በኩል  የመቐለ ከተማው ጋይሳ አፖንግን ተክቶ በፊት አጥቂነት የሚሰለፈው (በግምታዊ አሰላለፍ – አቼምፖንግ አሞስ/አማኑኤል ገ/ ሚካኤል) ከወልዲያው አንዷለም ንጉሴ የተሻለ ነፃነት ያለው ይመስላል። ቡድኑ የማጥቃት ፍላጎት በሚያሳይባቸው ጨዋታዎች በጉዳት እና ቅጣት ሳቢያ ከአማካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ሲያገኝ የማይታየው የወልዲያ የተከላካይ ክፍል በመቐለ የፊት አጥቂ እና የአጥቂ አማካይ መሀከል ከሚኖሩ ቅብብሎች መነሻነት የግብ ሙከራዎችን ሊያስተናግድ ይችላል። ሰሞኑን ለ 4-3-3 በቀረበ ቅርፅ እየተመለከትነው ያለነው ወልድያ አማካይ ክፍል ላይ ሙሉ ለሙሉ መከላከሉን ሊያግዝ የሚችል አንድ ተጨዋችን በመጠቀም ሀብታሙ ሸዋለም ከማጥቃት ተሳትፎው ባለፈ ከዚህ ተጨዋች ጎን በመሆን ጫና እንዲቀንስ ሲጠቀምበት ይስተዋላል። ይህ አቀራረብ የመቐለ ከተማ ጠንካራ ጎን የሆኑትን በ4-2-3-1 ከአጥቂ አማካዩ ግራ እና ቀኝ የሚሰለፉ ተጨዋቾችን የማጥቃት ሀይል የመገደቡ ነገር አጠያያቂ ነው። በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች መሀከል በተከላካይ መስመሩና በሁለቱ የተከላካይ አማካዮቹ መሀል ክፍተትን የማይሰጠው መቐለ ከተማ በዚህም ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖረው የታመናል። በዚህ አኳኃንም አንዷለም ንጉሴ የሚያገኘው ክፍተት ጠባብ እንደሚሆን መናገር ይቻላል። እዚህ ቦታ ላይ የመቀባባያ ክፍተትን ለመፍጠር የወልዲያው የጨዋታ አቀጣጣይ ምንያህል ተሾመ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር የሚኖረው መግባባት እጅጉን ወሳኝ ይሆናል። በዚህ ውስጥም የመስመር አጥቂዎቹ ፍፁም ገ/ማርያም እና ያሬድ ብርሀኑ ቡድኑ የሜዳውን ስፋት ተጠቅሞ በተከላካዮች መሀል የሚኖረውን ክፍተት ለማስፋት እንዲችል የማድረግ ኃላፊነት ይኖራቸዋል። በአጠቃላይ ግን መቐለዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ የሚሳበውን የተጋጣሚያቸውን አቀራረብ መሰረት በማድረግ እና እንቅስቃሴዎችን በመቋረጥ በፍጥነት በኤሚክሪል ቤሊንጌ ፊት ለመገኘት እንዲሁም ወልዲያዎች ምንያህል ተሾመን ማዕከል ባደረገ የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *