የካፍ የልህቀት ማዕከል ቀጣይ እጣ ፋንታ በቅርቡ ይወሰናል

ካፍ በአዲስ አበባ ሲኤምኢሰ አከባቢ ግንባታው ተጅመሮ የተቋረጠውን የልህቀት ማዕከል ቀጣይ እጣ ፋንታ በቅረቡ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተነገረ፡፡ የልህቀት ማዕከሉ ከ14 ዓመታት በፊት ግንባታው ቢጀመርም በበጀት እጦት ምክንያት እስኳሁን ሳይጠናቀቅ በእንጥልጥል ላይ ቀርቷል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ ግንባታው ባለመጠናቀቁ ንብረቶቹ ለጉዳት የተጋለጡ ሲሆን የቀድሞ የካፍ ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ ግንባታው ለማጠናቀቅ ቃል ቢገቡም ቃላቸው ሳይፈፀም ቀርቷል፡፡ የካፍ ፕሬዝደንት የሆኑት አህመድ አህመድ በነሃሴ 2009 ላይ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት በጀት ለመልቀቅ አስቀድሞ ኦዲት መደረግ እንዳለበት ማስገንዘባቸው ይታወቃል፡፡ የፋይናንስ ግልፅነት መኖሩ አስፈላጊ ስለሆነ ከአሁን በኃላ የሚለቀቁ ገንዘቦች ኦዲት ተደርገው መሆን አለባቸው ያሉት አህመድ ከወራት ቆይታ በኃላ ውሳኔ ለመስጠት እንዲስችላቸው ግብፃዊ መሃንዲስ አርብ ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ ታውቋል፡፡

መሃንዲሱ ማዕከሉ ያለበትን ደረጃ ከተመለከተ በኃላ ካይሮ በማቅናት ለካፍ ሪፖርት የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ ግንባታውም ከቆመበት የሚቀጥልበት መንገድን አቅጣጫ እንደሚያሲዝ እና በጀትም ለዚህ ማስፈፀሚያ ሊለቀቅ እንደሚችል የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በካሜሮን የተገነባው ተመሳሳይ የልህቀት ማዕከል ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በሴኔጋል እና ኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙት ማዕከላት ግን ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ ስራ መጀመር አልቻሉም፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው ማዕከል የመጀመሪያው ዙር ግንባታው ቢጠናቀቅም በግዜ ብዛት ግንባታው የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ የመጫወቻ ሜዳዎች እና ሌሎች አስፈላጊ የማዕከሉ ክፍሎች ግን ግንባታቸው አልተጀመረም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *