​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | አአ ከተማ ሲያሸንፍ ሰበታ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 10ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው አአ ከተማ ልዩነቱን ያሰፋበትን ድል ሲያስመዘግብ ፌዴራል ፖሊስ እና ቡራዩ ከተማም ድል ቀንቷቸዋል።

ወደ ኮምቦሎቻ ያመራው አዲስ አበባ ከተማ ወሎ ኮምቦልቻን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የዋና ከተማውን ክለብ ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው አጥቂው ፍቃዱ አለሙ ነው።

ለገጣፎ ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ከሚገኙት ክለቦች መካከል የሆኑት ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

በኦሜድላ ሜዳ አክሱም ከተማን ያስተናገደው ፌደራል ፖሊስ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና የመውጣት ተስፋውን አለምልሟል። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት አክሱም ከተማዎች ቢሆኑም የጠራ የጎል አጋጣሚ በመፍጠር ረገድ ሲቸገሩ ታይተዋል። በፌዴራል በኩል በ30ኛው ደቂቃ ሊቁ አልታየ የሞከረው እንዲሁም የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሳሙኤል ብርሃኑ የአክሱምን ግብ ጠባቂ በማለፍ ኃይል ቀሌቅሎ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ጨርፋ ወጥታለች፡፡

ከዕረፍት መልስ ተጭነው የተጫወቱት ፌዴራል ፖሊሶች በ66ኛው ደቂቃ ሊቁ አልታየ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አብዱራሂም ዘይን ወደ ግብነት ለውጦ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኃላም ፌዴራሎች አፈግፍገው በመጫወት ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል፡፡

ቡራዩ ላይ ኢኮስኮን ያስተነናገደው ቡራዩ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። በ57ኛው ደቂቃ ላይ በኢኮስኮ የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኢሳይያስ ታደሰ ወደ ግብነት ለውጦታል፡፡

በያያ ቪሌጅ ሜዳ ሱሉልታ ከተማ ከ የካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቀቀል። የካዎች በእዮብ ዘይኑ አማካይነት ቀዳሚ ሲሆኑ በ32ኛው ደቂቃ ጌታሁን ሙሉጌታ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤርሚያስ ዳንኤል ወደ ግብነት ለውጦ አቻ ሆነዋል። ቶሎሳ ንጉሴ ደግሞ በ43ኛው ደቂቃ ሱሉልታን ወደ መሪነት አሸጋግሮ የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ ከዕረፍት መልስ የካ ክፍለ ከተማ በ68ኛው ደቂቃ አለማየው አባይ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

በዚህ ምድብ ሊደረጉ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል ባህርዳር ከተማ ከ አውስኮድ በቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ምክንያት ፤ የኢትዮጵያ መድን እና ደሴ ከተማ ጨዋታ ደግሞ መድን በፌዴሬሽኑ በመታገዱ ሳይደረጉ ቀርተዋል። እሁድ ነቀምት ላይ ሊካሄድ የነበረው የነቀምት ከተማ እና ሽረ እንዳስላሴ ጨዋታ ደግሞ ሰኞ በ09:00 ሰበታ ላይ የሚደረግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *