​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ኤሪክ ሙራንዳ እና ደቡብ ፖሊስ በግብ ተንበሻብሸዋል

በምድብ ለ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 10ኛ ሳምንት እሁድ 6 ጨዋታዎች ተደርገዋል። ደቡብ ፖሊስ በሜዳው ጎል ማዝነቡን ሲቀጥል ሀዲያ ሆሳዕና ፣ ስልጤ ወራቤ ፣ ቡታጅራ እና ወልቂጤም አሸንፈዋል።

ደቡብ ፖሊስ 5-1 ካፋ ቡና

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ሀዋሳ ላይ ተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ በኤሪክ ሙራንዳ ሐት-ትሪክ ታግዞ ካፋ ቡናንን 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ካፋ የግብ ክልል አጋድለው የተጫወቱት ደቡብ ፖሊሶች በ11ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ አበባየሁ ዮሀንስ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ ጀ ግብነት በቀየረው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። በ20ኛው ደቂቃ ቢንያም አድማሱ፣ ብርሀኑ በቀለ እና አበባየሁ ዮሀንስ በግሩም ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው ያመከኑት በደቡብ ፖሊስ በኩል ሲጠቀስ በ29ኛው ደቂቃ ላይ ካፋዎች በኡጁሉ ኦኬሎ አማካኝነት ያገኙዋትን ግልፅ የግብ እድል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲልም አበባየሁ ዮሀንስ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አክሎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ 68ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና አጥቂ ኬኒያዊው ኤሪክ ሙራንዳ መፍጠር ችሏል። በ72ኛው ደቂቃ ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ገብቶ የፓሊስን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ ሲያደርግ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከአበባየሁ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል የካፋ የግብ ክልል ይዘው የገባውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ልዩነቱን ወደ 4 ሲያሰፋ በ81ኛ ደቂቃ ደግሞ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል።

ካፋ ቡናዎች በአንተነህ ከበደ አማካኝነት በ85ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ቢያስቆጥሩም ጨዋታው በደቡብ  ፓሊስ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ወደ ሻሸመኔ ከተማ ያቀናው ወልቂጤ ከተማ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ሻሸመኔ ከተማን 2-0 አሸንፎ ተመልሷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ከዕረፍት መልስ በ60ኛው ደቂቃ ፍቅሩ እና በ65ኛው ደቂቃ አትክልት ንጉሴ ያስቆጠሯቸወ ጎሎች እንግዶቹን ወደ ድል መርቷቸዋል።

ወደ መቂ ያመራው ናሽናል ሴሜንት ኸይረዲን ጀማል በ62ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ መቂ ከተማን 1-0 ሲያሸንፍ ስልጤ ወራቤ ወደ ነገሌ አምርቶ ነገሌ ከተማን 1-0 በመርታት ደረጃውን ማሻሻሉን ቀጥሏል። የስልጤን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ገብረመስቀል ዱባለ ነው።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ድሬዳዋ ፖሊስን አስተናግዶ ኤፍሬም ቶማስ በ34ኛው እና ክንዴ አቡቹ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 አሸንፏል። ሆሳዕና ላይ ቤንች ማጂ ቡናን ያስተናናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በኢብሳ በፍቃዱ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

በዚህ ምድብ ዛሬ አንድ ጨዋታ ሲደረግ የምድቡ መሪ ዲላ ከተማ 08:00 ላይ ሀላባ ከተማን ያስተናግዳል። ሀምበሪቾ ከጅማ አባ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ሀምበሪቾ በሜዳው ሁለት ጨዋታ እንዳያደርግ የተጣለበትን ቅጣት ይግባኝ በመጠየቁ የማይካሄድ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *