አሰልጣኝ ብርሀኔ ገብረግዚአብሔር ከወልዋሎ ጋር ተለያዩ

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደጉት እና በፕሪምየር ሊጉ መልካም አጀማመር አድርገው የነበሩት አሰልጣኝ ብርሀኔ ገብረግዚአብሔር ከክለቡ ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው ተረጋግጧል።

ወልዋሎ በመጀመርያዎቹ 5 ሳምንታት መልካም ጉዞ ካደረገ በኋላ በተከታታይ 7 ጨዋታዎች ከድል መራቁን ተከትሎ አሰሰልጣኙ ላይ በሚነሳው ተቃውሞ ደስተኛ እንዳልሆኑ እና ሁኔታዎች የማይስተካከሉ ከሆነ እንደሚለቁ ከወላይታ ድቻ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ክለቡ ያቀረቡትን የልቀቁኝ ጥያቄ ትላንት ምሽት ባደረጉት ስብሰባ በመቀበል በስምምነት ተለያይተዋል።

አሰልጣኝ ብርሀኔ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በክለቡ የተደረገባቸው ጫና ስራቸውን ለመልቀቅ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል።

” በክለቡ ውስጥ የአመራር መለዋወጥ በስራዬ ላይ ተፅኖ አድርጎብኛል። በአግባቡም መስራት አልቻልኩም። የሚወደኝ ህዝብ ሁሉ እንዲጠላኝ ተደርጓል። የትኛውም ቡድን እንደ አዲስነቱ በሊጉ መቆየትን እንጂ በመጣበት አመት ዋንጫ እንዲያነሳ አይገደድም። የውጭ ተጫዋቾች ተባለ መጣ። ተጫዋቾች ይገዙ ተባለ መጡ። አሁን ደግሞ ያልሆኑ ድርጊቶችን እና ስድቦችን መቋቋም ፀባዬ አይደለም። እኔ በነፃነት መስራትን እንጂ ማንም እንደፈለገው ሊያዘኝ አይችልም። እግር ኳስ ነፃነት ይፈልጋል። ያን ከገዜ ወደ ጊዜ አጥቻለው። 

 “እኔ የገነባሁት ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን ነበር። ያን የሚፈልግ ክለብ ካለ በቀጣይ የምሄድ ይሆናል። ለጊዜው ግን እያሰብኩ እቆያለሁ። ” ብለዋል
አሰልጣኝ ብርሀኔ በቀጣይ ከድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝነት ጋር ስማቸው የተያያዘ ሲሆን ወደ ምስራቃዊቷ ከተማ ክለብ የማምራት እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል። አሰልጣኙም ከድሬዳዋ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል። 

ወልዋሎ በቀጣይ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከአምስት ያላነሱ አሰልጣኞችን መያዙ የተነገረ ሲሆን እስከዛው ድረስ በረዳት አሰልጣኙ ሀፍቶም ኪሮስ የሚመራ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *