ወንድወሰን ገረመው በዘንድሮው የውድድር ዓመት በመደበኛነት እየተሰለፉ ከሚገኙ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነው፡፡ አምና በፍፃሜው ወሳኝ የመለያ ምቶችን በማዳን ወላይታ ድቻን ለጥሎ ማለፍ ድል ያበቃው ወንድወሰን ዘንድሮም በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ፣ ስለ ቀድሞ ክለቡ እና ስለ ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡
አምና ወላይታ ድቻ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዲያነሳ እና ክለቡ በሊጉ ሳይወርድ እንዲቆይ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበርክ፡፡ እንዴት ነበር የአምናው የውድድር ቆይታህ ?
አምና ከተለያዩ ተፅዕኖዎች ወጥቼ ትልቁን አቅሜን ያሳየሁበት ፤ በራስ መተማመኔ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ፤ ራሴን መልሼ በሚገባ ያገኘሁበት አመት ነበር፡፡ ክለቤን ከመውረድ አደጋ ያተረፍኩበት እንዲሁም በክለቡ ታሪክ ተሳክቶ የማያውቀውን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዳነሳ አድርጎኛል፡፡ ይህም ለእኔ ትልቅ ክብር ነው። እድለኛ ነኝ ፤ የኢትዮዽያ ፕሪምየር የሊጉ ዋንጫ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ደግሞ ከወላይታ ድቻ ጋር ማንሳት ችያለው።
አምና ጥሩ አቋም እንደማሳየትህ ዘንድሮ ክለቡ የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂ (ፌቮ ኢማኑኤል) ማምጣቱን እንዴት ታየዋለህ?
ክለቡ በዘንድሮ አመት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች አሉበት፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ክለቡ በታሪኩ አስፈርሞ የማያውቀውን የውጭ ሀገር ተጨዋቾች አስፈርሟል፡፡ ቡድኑን ለማጠናከር እና ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ በማሰብ የውጭ ተጨዋች ፈረመ እንጂ የእኔ አቋም በመውረድ አይደለም፡፡ ክለቡም ሆነ ደጋፊው በእኔ በጣም ደስተኛ ናቸው። በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ሁለት ጠንካራ ግብ ጠባቂ ቢኖር ጥሩ ነው። ያም ቢሆን አብዛኛውን ጨዋታ በቋሚነት እየተሰለፍኩ የምገኘው እኔ ነኝ፡፡ ይህ የሆነውም የውጭ ግብ ጠባቂ ስለመጣ ሳይሆን የእኔ አቅም የተሻለ ስለሆነ ነው።
በተለያየ አመት ሁለት ጊዜ በኢትዮዽያ ቡና የመጫወት እድል አግኝተህ በተለያዩ ምክንያቶች ከክለቡ ጋር ተለያይተሀል የወጣህበት መንገድ አሳማኝ ነው ትላለህ?
ከኢትዮዽያ ቡና የምወጣባቸው መንገዶች ሁሉ አሳማኞች አልነበሩም፡፡ ምንም በቂና ተጨባጭ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ነው የወጣሁት፡፡ በ2003 ቻምፒዮን ከሆንን በኋላ 2004 ላይ በአሰልጣኙ የግል አመለካከት የተነሳ ከእግርኳስ እንድገለል ሆኖ እስከ መታገድ እና መልቀቂያ እስከ አለመስጠት የደረሰ ነበር። አንድ ሰው ክለቡን በሚገባ አገልግሎ እየጠቀመ ሳለ መብቱ ሲነካ የተለያዩ መንገዶች ይሄዳል፡፡ እኔም በተደጋጋሚ ችግሩ እንዲፈታ ቡና ፅህፈት ቤት ፣ ቦርዱ ጋር ፣ ፌዴሬሽን ሁሉ ሞክሬ ሳይስተካከል ሲቀር መብቴን ለማስከበር ፍትህ ለማግኘት ወደ ፍርድ ቤት አምርቼ ከአንድ አመት ተኩል ክርክር በኋላ ውሳኔ አግኝቼ ወደ ቡና እንዲመለስ ብደረግም ከክለቡ ስራ አሰኪያጅ በስምምነት መልቀቂያዬን ተቀብያለው፡፡ ወደ ፊት ጥሩ ከሆንኩ እመለሳለው ብዬ ነው የወጣሁት። ከዚህ በመቀጠል እንደገና በጥሩ አቋም በመገኘቴ እና የመጫወቱም ፍላጎት ስለነበረኝ በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ጥሪ ቀርቦልኝ መጫወት ብጀምርም ቡናን በፍርድ ቤት ድረስ የከሰሰ ተጨዋች እንዴት ወደ ቡና ተመልሶ ይመጣል በማለት በአንዳንድ ደጋፊዎች ያልተገባ ተቃውሞ እና ጫና በሜዳ ላይ ጥሩ እየሰራው እንኳ በቡና ማልያ ታሪክ መሰራቴን እየታወቀ በጥላቻ ይቃወሙኝ ጀመር፡፡ ይህ የመጫወት ክለቡን የማገልገል ፍላጎቴ እየወረደ መጥቶ በስምምነት ኢትዮዽያ ቡናን ለቅቄ ወደ ወላይታ ድቻ ላመራ ችያለው።
ከዚህ በኋላ በድጋሚ በኢትዮዽያ ቡና የመጫወት እድል ብታገኝ ተመልሰህ ትጫወታለህ ?
አዎ ኢትዮዽያ ቡና ክብር ፣ እውቅና ያገኘሁበት ቤት ነው። ኢትዮዽያ ውስጥ ካሉ ክለቦች ትልቁ ክለብ ነው። እድሉን ባገኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደ ፊትም በድጋሚ መጥቼ እንደምጫወት እርግጠኛ ነኝ፡፡ በአሁን ሰአት ምርጥ አቋሜ ላይ እገኛለሁ፡፡ የተሻለ ደረጃ ላይ ከመገኘቴ ባሻገር በቂ ልምድ እያገኘው በመሆኔ አንድ ቀን ተመልሼ በመግባት ሌላ ታሪክ በድጋሚ እሰራለው ብዬ አስባለው። ይህም እሩቅ አይሆንም ምክንያቱም ኢትዮዽያ ቡና ክለብን እወደዋለሁ።
በዋና ውድድሮች ላይ በኢትዮዽያ እግርኳስ ታሪክ አንድ የውጭ ሀገር ግብጠባቂን ኢትዮዽያዊ ግብ ጠባቂ በጥሩ አቋሙ በተቀያሪ ወንበር አስቀምጦ በቋሚነት ሲሰለፍ አልተለመደም፡፡ ይህ የሚፈጥርብህ ስሜት አለ?
አዎ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? የውጭ ግብ ጠባቂ ስለሆነ ብቻ ቅድሚያ ተሰጥቶት ስህተቶችን እየሰራ የተሻለ እንቅስቃሴ ሳያሳይ ቀርቶ ተደጋጋሚ የመሰለፍ እድል ተሰቶት ነበር። አሁን ግን አሰልጣኙ ተገዶ ለእኔ እድል በመስጠቱ እና እኔም ሜዳ ላይ በጠንካራ አቋም መቅረቤ እና ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረኩ ቡድኑን ይዤ በመውጣቴ እድሉን እያገኘው ነው። የውጭ ዜጋ ግብ ጠባቂ በተቀያሪ ወንበር ላይ ማስቀመጤን ለራሴ ክብር እሰጠዋለው፡፡ ከእሱ የተሻለ አቅም እንዳለኝ ማሳየቴ ለሌሎችም ኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች አርዓያ ይሆናል ብዬ አስባለው፡፡ ለሌሎች አሰልጣኞች ትምህርት ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ ላለው የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች እጥረት አንድ መፍትሄ ይሰጣል ብዬ ነው የማስበው። ለኢትዮዽያውን ግብ ጠባቂዎች እድል ከተሰጣቸው እና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ከተደረገ መስራት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ።
ኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች በዋናው ሊግ እየጠፉ ነው፡፡ ክለቦች ኢትዮዽያዊ ግብ ጠባቂ እየፈለጉ ያሉት ለዋና ግብ ጠባቂነት ሳይሆን ለሁለተኛ እና ሦስተኛ ግብ ጠባቂነት ነው፡፡ ይህ እንደ አንድ ግብ ጠባቂ ያሳስብሃል?
ይህ ለሀገር ጠንቅ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ለውጭ ግብ ጠባቂዎች ብቻ ትኩረት እየሰጠህ ከሆነ ሀገርህን እየገደልክ ነው። ሌላው እያንዳንዱን ስህተት በግብ ጠባቂ የማሳበብ ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሊታረም ይገባል። የቡድንህን ቅርፅ ከተከላካይ እስከ አጥቂ በደንብ ቡድኑን አጠናክረህ ካልሰራህ ፣ የምተከተለው የጨዋታ አቀራረብ አዋጪ ካልሆነ ግብ ጠባቂ ብቻውን ምንም ሊያመጣ አይችልም። ጥሩ ቡድን ከሰራህ የተኛውም የሀገር ውስጥ ሆነ የውጭ ግብ ጠባቂ ቢገባ ጎልቶ ይወጣል። ኢትዮዽያ ውስጥ የጠፋው ጥሩ ግብ ጠባቂ ሳይሆን አዕምሯቸውን ጠብቆ ፣ ጠንካራ ቡድን ተሰርቶ ፣ በቂ የሆነ ስልጠና ተሰጥቶ ከተኬደ የግብ ጠባቂ ችግር የሚታሰብ አይሆንም ።
በኢትዮዽያ ውስጥ ያሉ የውጭ ግብ ጠባቂዎች ስለ ኢትዮዽያውያን ግብ ጠበቂ ሲናገሩ ጥሩ አቅም እንዳላቸው ሆኖም ልምምድ ላይ ሰነፍ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ለማወቅ እና ለመለወጥ ከመጣር ይልቅ አይተጉም ይላሉ፡፡ አንተ በዚህ ትስማማለህ?
እውነት ለመናገር ከልምምድ ስጀምር አብዛኛዎቹ የውጭ ግብ ጠባቂዎች ጠንከር ያለ ልምምድ ሲሰጥ አመመኝ ብሎ የመቅረት በትክክል ልምምድ ያለመስራት ልማድ ነው ያላቸው፡፡ ለምሳሌ አጠገቤ ያለው የውጭ ዜጋ (ፌቮ) ከሳምንቱ የልምምድ ጊዜ አራቱን ቀን አመመኝ ብሎ ልምምድ የማይሰራ ነው፡፡ ሀሪሰንን አይቻለው፡፡ ከዚህ በፊትም ሙስጠፋን (በ2003 ለቡና የተጫወተ ናይጄርያዊ) አይቻለው፡፡ አብዛኛዎቹ በተፈጥሮ ጠንካራ ቢሆኑም የስራ ፍላጎታቸው ግን የወረደ ነው ። ይህም ቢሆን እኛ ጋር ችግር የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ለሁሉም ጨዋታዎች እኩል ግምት ከመስጠት ይልቅ ጨዋታዎችን የመምረጥ ስህተት አለ፡፡ ይህ የአቋም መውረድን ሊያመጣ ይችላል። እኔ ብዙ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂ አይቻለው፡፡ ልምምዱን በአግባቡ የማይሰራ የለም፡፡ ነገር ግን ካለፍንበት መንገድ አኳያ የሚያበላልጠን ነገር ይኖራል፡፡ ሮበርት እና ሀሪሰን ጥሩ አቅም ያላቸው ቢሆንም ከዛ ውጭ የምተማመንበት በረኛ የለም፡፡ እነሱ ያለፉበት የስልጠና መንገድ ጥሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እስቲ የእኛ ሀገር የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ስልጠና የማግኘት እድላቸው ጠባብ ነው፡፡ እንደውም የለም ማለት ይቻላል። ይህም ነው የግብ ጠባቂ እጥረት እንዲኖር ያደረገው።
የክለብ ደጋፊዎች ኢትዮዽያዊ ግብ ጠባቂ በሚደግፉበት ክለብ ውስጥ በቋሚ ተሰላፊነት ገብተው እንዲጫወቱ እንደማይፈልጉ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህን አንተ እንዴት ታየዋለህ?
ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እንደሚባለው ነው፡፡ ይህን የምልህ ለምሳሌ ኢትዮዽያ ቡና ሁሌ የዋንጫ አሸናፊ የማይሆነው የበረኛ ችግር ስላለበት ነው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ሀሪሰን ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው ፤ ነገር ግን ሀሪሰን ከመጣ ጀምሮ ምንም ዋንጫ አላገኙም፡፡ የግብ ጠባቂ ከሆነ ችግሩ ጥሩ በረኛ መጥቶ ለምን ዋንጫ አያነሳም? የግብ ጠባቂ ችግር ሳይሆን ሌላ መሰረታዊ ችግር አለ ማለት ነው። ስለዚህ ለኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች የምንሰጠው ግምት ከፍ ሊል ይገባል፡፡ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር ቢደረግ የመሰለፍ እድል የሚሰጣቸው ከሆነ ከውጭዎቹ ግብ ጠባቂዎች የተሻለ መስራት ይችላሉ።