​ሪፖርት | አፄዎቹ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

በጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲየም በተደረገው 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግሟል።

ባለሜዳዎቹ ባለፈው ሳምንት ይርጋለም ላይ በሲዳማ 3-0 ከተሸነፈው ስብስብ መካከል ዳዊት  እስጢፋኖስ እና ፍፁም ከበደ በይስሀቅ መኩርያ እና ኤፍሬም አለሙ ምትክ በመጀመርያ አሰላለፍ ሲካተቱ በኤሌክትሪክ በኩል በ11ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ በምንያህል ይመር እና ተክሉ ተስፋዬ ምትክ በኃይሉ ተሻገር እና ዘካርያስ ቱጂን ወጀ መጀመርያ አሰላለፍ በመመለስ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች ተጭነው መጫወት ቢችሉም የፈጠሯቸውን የጎል እድሎች ወደ ግብነት መለወጥ ተስኗቸው ታይተዋል። ራምኬል ሎክ በ12ኛው ፣ 24ኛው እና 27ኛው ደቂቃዎች ፣ ፊሊፕ ዳውዝ በ15ኛው ደቂቃ እና ፍፁም ከበደ በ38ኛው ደቂቃ የሞከሯቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በዲዲዬ ለብሪ እና አልሀሰን ካሉሻ አማካኝነት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። በፈጣን የማጥቀች ሽግግር ያገኙትን ኳስ ወደ ፋሲል የግብ ክልል በሚያመሩበት ጊዜም በዲዲዬ ለብሪ ላይ ጥፋት ተሰርቶ በዝምታ መታለፉን በመቃወም ጨዋታውን አቋርጠው ክስ አስመዝግበዋል።

ከተወሰኑ ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ በተጀመረው ጨዋታ ፋሲል የተሻለ በመንቀሳቀስ ተጭኖ ቢጫወትም ተጨማሪ ሙከራዎች ሳይታዩ የመደመርያው አጋማሽ ያለጎል ተገባዷል።
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደመጀመርያው ሁሉ በፋሲል የበላይነት የቀጠለ ሲሆን በመጀመርያዎቹ 5 ደቂቃዎች ውስጥም ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ46ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከዳዊት እስጢፍኖስ የተሻገረለትን ኳስ ሲያመክናት ፣ በ47ኛው ደቂቃ ፊሊኘ ዳውዝ እና በ48ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

በ52ኛው ደቂቃ ከ4 ጨዋታ ቅጣት የተመለሰው አብዱራህማን ሙባረክ ኤርሚያስ ኃይሉን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ለመሆንም በቅቷል። በ86ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ኄኖክ ገምተሳ ያሻገረውን ኳስ አብዱራህማን በግምባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሯል።

ኤሌክትሪኮች ጎሉ ከመቆጠሩ በፊት በፋሲል የግብ ክልል ጥፋት ተፈፅሞ በአርቢትሩ በቸልታ ታልፎ ለጎሉ መቆጠር መንስኤ ሆኗል በሚል በጨዋታው ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ያስመዘገቡ ሲሆን ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የአሰልጣኞች  አስተያየት 

ምንተሰኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

እኛ የምንተወቀው በኳስ ፍሰታችን ነው። በሜዳችን ከመሆኑ አንፃር ተጫዋቾቻችን ተረጋግተው ሲጫወቱ ነበር። ቢሆንም ብዙ የጎል እድሎችን ፈጥረን ያገባንው አንድ ጎል ብቻ ነው። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል መመለስ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በቀጣይ የቀሩን ሁለት የአንደኛ ዙር ጨዋታዎችን በድል ለማጠናቀቅ ጠንክረን እንሰራለን።

አሸናፊ በቀለ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ 

ከጨዋታው በኋላ በሁለቱ ክለቦች ቡድን መሪዎች በተፈጠረው አለመግባባት የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተጫዋቾችን እና የቡድን አባላቱን በማረጋጋት ላይ ስለነበሩ አስተያየት ሳይሰጡ ቢቀሩም ሶከር ኢትዮጵያ አሰልጣኙን በስልክ አናግራለች።

“ስለ ጨዋታው መናገር በፍፁም አልፈልግም። የዳኝነቱ በደል አሳሳቢ ነው። ብትናገርም ችግሮች ይገጥሙሀል። ለኔ ከመናገሩ ዝምታን መምረጡ የተሻለ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ብናገርም እንደሰበብ ስለሚቆጠርብኝ መናገር አልፈልግም። ውጤቱ እንደማይገባን የጎንደር ህዝብ እና ተመልካች ይፈርዳል። ከኔ በተሻለ ከእነሱ መስማቱ የተሻለ ሆኖ ይሰማኛል”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *