ሪፖርት| የደደቢት ተከታታይ የአሸናፊነት ጉዞ በጅማ አባጅፋር ተቋጨ

የ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲደረግ ጅማ አባ ጅፋር መሪው ደደቢትን 2-1 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።

ደደቢት ጉዳት ባጋጠመው ስዩም ተስፋዬ ምትክ ኮዌኪ አንዶህን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ በማስገባት ደስታ ደሙን ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት ቦታ የወሰደ ሲሆን በተለመደው የ4-3-3 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመረው። በተመሳሳይ ኦኪኪ አፎላቢን እና መላኩ ወልዴን በጉዳት መጠቀም ያልቻሉት ጅማ አባ ጅፋሮች ቢኒያም ሲራጅን እና ሳምሶን ቆልቻን በምትካቸው በማስገባት እንዲሁም ቅርፃቸውን ወደ 4-2-3-1 በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል። የአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳም ላለፉት ሁለት ሳምንታት ጨዋታ ሳያስተናግድ በመቆየቱ ወደ አረንጓዴነቱ ተመልሶ ነበር የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ያስተናገደው።

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ጅማ አባ ጅፋሮችም ተጋጣሚያቸውን ለማስጨነቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ገና በሁለተኛው ደቂቃ ደደቢቶች ካገኙት የማዕዘን ምት ኳስ መንጠቅ የቻሉት ጅማዎች በዮናስ ገረመው አማካይነት ኳሱን በፍጥነት ለሳምሶን ቆልቻ ማድረስ ቢችሉም ሳምሶን የግብ ክልሉን ለቆ በወጣው ክሌመንት ላይ ሊያስቆጥር የሚችልበትን ዕድል መጠቀም አልቻለም። ሆኖም አራተኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር የጀመረውን ጥቃት ዮናስ ገረመው በግራ መስመር አማካይነት ጨዋታውን ለጀመረው ተመስገን ገ/ኪዳን አሳልፎለት ተመስገን በጥሩ አጨራረስ ዕንግዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። 

ግብ ካስቆጠሩ በኃላም ሙሉ ለሙሉ ጫና ፈጥረው እና ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል አመዝነው መጫወታቸውን የቀጠሉት አባ ጅፋሮች በግራ መስመራቸው በኩል የተጨዋቾች ሽግሽግ የተደረገበትን የደደቢት የቀኝ ተከላካይ ክፍል መረበሻቸውን ቀጥለዋል። የወሰዱትን ብልጫም ተከትሎ 17ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው ከሳምሶን ቆልቻ የተቀበለውን ኳስ ከርቀት መቶ በማስቆጠር መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። በፍጥነት በተቆጠሩባቸው ግቦች የተደናገጡ የሚመስሉት ደደቢቶች ወደ ጨዋታው ከመመለሳቸው በፊት 21ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ሔኖክ ኢሳያስን በእጁ በመማታቱ እና በፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው የቀይ ካርድ በመመልከቱ ተጨማሪ ጫና ውስጥ እንዲገቡ ሆኗል። ከጌታነህ ቀይ ካርድ በፊትም የመስመር አጥቂዎቹ ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ያለው በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴን ተከትሎ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ተወስዶበት የነበረው ደደቢት ከቀይ ካርዱ በኃላ ደግሞ አማካይ ክፍል ላይ ይበልጥ አቅም ሲያጣ ተስተውሏል። አጋጣሚውን በሚገባ የተጠቀሙበት አባ ጅፋሮች የሜዳውን ቁመት እና ስፋት በጥቅም ላይ ባዋለ የተረጋጋ የኳስ ቅብብል ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ በጨዋታው የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። አባ ጅፋሮች በእነዚህ ደቂቃዎች ከነበራቸው ብልጫ አንፃር ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ተጨማሪ ግቦችን በማስቆጠሩ በኩል ባይሳካላቸውም ደደቢቶች ሙሉ ለሙሉ ከጨዋታው መንፈስ ውጪ እንዲሆኑ እና የተጨዋቾቻውም የቦታ አያያዝ እጅግ የተዛባ እንዲሆን ያደረጉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል። እግራቸው ላይ ኳስ ይዘው መቆየት የተቸገሩት ደደቢቶች በበኩላቸው 35ኛው ደቂቃ ላይ ከኩዌኪ አንዶህ በተነሳ ቅጣት ምት እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ በሽመክት ጉግሳ እና የአብስራ ተስፋዬ አማካይነት በተፈጠሩ ዕድሎች ልዩነቱን ለማጥበብ ቢቃረቡም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ሂደት ከመጀመሪያው ፍፁም የተለየ ነበር። አባ ጅፋሮች በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸውን ብልጫ እና ልዩ የኳስ ፍሰት ይልቅ ወደ ራሳቸው ሜዳ ተስበው በመከላከል ውጤቱን ማስጠበቅን መርጠዋል። አንድ ሰው የጎደለባቸው ደደቢቶች ደግሞ የረዥም ጊዜ ልምድ ባለቤቶቹን ኤፍሬም አሻሞ እና ብርሀኑ ቦጋለን ቀይረው በማስገባት ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ ተመስርተው ከመልበሻ ክፍል ተመልሰዋል። በዚህም መሰረት ደደቢቶች ሶስት ተከላካዮችን ከኃላ በማስቀረት በተለይም በቀኝ መስመር ከኩዌኪ አንዶህ ወደ ሳጥን ውስጥ በሚጣሉ ረዣዥም ኳሶች አጋዥነት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መሰንዘር ጀመሩ። ከመሰል እንቅስቃሴዎች በመነሳት በኤፍሬም አሻሞ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጥለውም 62ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የመጣን ኳስ ክዌኪ አንዶህ በግንባሩ ወደ ግብ ሲሞክር ሔኖክ አዱኛ ከመስመር ላይ ኳስ በእጁ በማውጣቱ የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ሔኖክም በቀይ ካርድ ከሜዳ ለመሰናበት ተገዷል። 

ፍፁም ቅጣት ምቷን ኤፍሬም ወደ ግብነት ከቀየራት በኃላ የደደቢት ጫና እጅግ በርትቶ ታይቷል። 55ኛው ደቂቃ ላይ በደስታ ደሙ እና ክሌመንት አዞንቶ አለመግባባት ምክንያት ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች አጋጣሚውን በተመስገን አማካይነት መጠቀም ባይችሉም በሌሎች በርካታ ጊዜያት ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ተፈጥረውላቸው ነበር። ሆኖም በደደቢት ሜዳ ላይ በቁጥር እጅግ ተመናምነው መታየታቸው ወደ ሶስተኛ ግብነት የሚቀየር ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ሰዐት በገፋ ቁጥርም የጥንቃቄያቸው መጠን ከፍ እያለ እና ከማጥቃት መንፈስ እየወጡ በተጨዋቾች የግል ጥረት ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች ውጪ እንደ ቡድን ጫና መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቃራኒው የተጋጣሚያቸው ማፈግፈግ የራስ መተማመናቸውን ከፍ ያረገላቸው ደደቢቶች ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ከነዚህ ውስጥ 69ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮ በተከላካዮች ተጨርፎ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ሲሆን አቤል ያለው 83ኛው ደቂቃ ላይ በሽመክት እና አስራት ጥሩ ቅብብል በቅርብ ርቀት ካገኘው አጋጣሚ እንዲሁም በመጨረሻ ደቂቃዎች ከደስታ ደሙ በቀኝ በኩል ከተሻገረ ኳስ የአቻነቷን ግብ አገኘ ተብሎ ቡጠበቀም ወጣቱ አጥቂ ሳይሳካለት ቀርቷል። በዚህ አኳኃን እስከ ጨዋታው ማብቂያ ድረስ በጥልቀት ተከላክለው የጨረሱት ጅማ አባ ጅፋሮች መሪነታቸውን ምማስጠበቅ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻለውን የሊጉን መሪ ድል ማድረግ ችለዋል።


የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ – ደደቢት

ጨዋታው ጥሩ ነው። ምንም አይደለም። ማሳበብ ባልፈልግም በዳኛ ተሸንፈናል። የተሰጠብን ቀይ ካርድ በፍፁም መረጃ የሌለው ነበር። ዳኛው የነበረበት ቦታ እና ጥፋት የተሰራበት ቦታ ርቀት አግባብነት የሌለው ነው። በተረፈ ተጨዋቾቼ ባደረጉት እንቅስቃሴ ብዙ መስዋትነት ከፍለዋል ብዙ የግብ ዕድሎችንም አግኝተዋል።

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር። ለኛም ለእነሱም ወሳኝ ነበር። እነሱም መሪ በመሆናቸው እኛም በተወሰነ መልኩ ወደ ላይ ለመጠጋት የሚያስችለን ጨዋታ ስለነበር በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ወደ ጎል ሄደናል ውጤታማም ሆነን ጎሎች አስቆጥረናል። ያንን ውጤት ይዘን ለመውጣት ስንል ከእረፍት በኃላ ትንሽ ተቸግረን ነበር። ነገር ግን በጥቅሉ ሲታይ ውጤታማ ነበርን። በዚህም በጣም ደስ ብሎናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *