ኢትዮጵያኖቹን የሚያገናኘው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ነገ ይደረጋል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታ ፔትሮጀት ስሞሃን ያስተናግዳል፡፡ በጨዋታውም ላይ ሁለቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ሽመልስ በቀለ እና ኡመድ ኡኩሪ ተቃራኒ ሆነው ይጋጠማሉ፡፡ በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ፔትሮጀት ጥሩ መሻሻሎችን ካሳየው ስሞሃ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ አርብ ምሽት ነው የሚካሄደው፡፡

በ21ኛው ሳምንት ስሞሃ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ዋዲ ደግላን ገጥሞ 2-1 የረታ ሲሆን ፔትሮጀት በበኩሉ ከታንታ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ስሞሃ ዋዲ ደግላን ሲረታ ኡመድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በውድድር አመቱ የተቀዛቀዘ የሆነውን ፔትሮጀትን የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ በታንታው ጨዋታ በአምበልነት መርቷል፡፡ ሽመልስ ላለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ፔትሮጀትን በአምበልነት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለቱም ተጫዋቾች በተደጋጋሚ በሊጉ ግብ በማስቆጠር የሚታወቁ ቢሆንም በንፅፅር በዘንድሮው የውድድር ዓመት ተቀዛቅዘዋል፡፡ በአጠቃላይም 4 ግቦች በድምር ያስቆጠሩበት ይህ የውድድር ዓመት ከዓምናው ጋር ሲነፃፃር የወረደ ነው፡፡ ሆኖም ተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ በቋሚ 11 ውስጥ ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ ግን አይስተዋልም፡፡

በአምስተኛው ሳምንት አሌክሳንደሪያ ላይ ስሞሃ እና ፔትሮጀትን ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ ኡመድ 90 ደቂቃ ሲጫወት ሽመልስ በበኩሉ በ82ኛው ደቂቃ በኢሳም ሶብሂ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ በአል ስዌዝ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስሞሃ ሁለተኛ ደረጃ ካለው ኢስማኤሊ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፔትሮጀት ደረጃውን ለማሻሻል ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት የግድ ይላቸዋል፡፡

ጨዋታውን በተመለከተ ኡመድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በጨዋታው ላይ ጥሩ ነገር እንደሚጠብቅ ተጠቁሟል፡፡ “ጨዋታው የሊግ እንደመሆኑ የተለየ ስሜት የለውም፡፡ ሽመልስ የሃገሬ ልጅ በመሆኑ በጨዋታው ላይ ጥሩ ነገር እንዲያደርግ ትመኛለህ፡፡ ከዚ ውጪ የስራ ጉዳይ ስለሆነ እኛም ለማሸነፍ እንጫወታለን፡፡ አስታውሳለው ኢትሃድ አሌክሳንደሪያ እያለው አል አሃሊን 4-1 ስናሸንፍ ሳላዲን ሰዒድ ተቀይሮ ገብቶ ያቺን ግብ ያስቆጠረብን፡፡ ግቡ ሲቆጠር እንደቡድን ጥሩ ስሜት ባይሰጥም ሳላ በማስቀጠሩ የተሰማኝ ስሜት አለ፡፡ ሰለዚህም ታቀራኒ ሆነህ ብትጋጠምም ጥሩ ነገር ለጓደኛህ ትመኛለህ፡፡”

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 12፡00 ላይ ይጀምራል፡፡ ሽመልስ ለተከታታይ አራተኛ ጨዋታ ፔትሮጀትን በአምበልነት እንደሚመራም ይጠበቃል፡፡ ጨዋታው በኦን ስፖርት፣ ናይል ስፖርት እና ዴኤምሲ ስፖርት የቀጥታ ስርጭት ያገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *