ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬደዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ከሊጉ መክፈቻ ጨዋታዎች መሀከል አንዱ የነበረው እና በይደር ተይዞ የቆየው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የድሬደዋ ከተማ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተደርጎ በሁለት የቅጣት ምት ጎሎች 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተገባዷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠመው ስብስቡ መሀከል ኢብራሒማ ፎፋናን ወደ ተጠባባቂ ወንበር አውርዶ ለጋዲሳ መብራቴ የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል በመስጠት በተለመደው የ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል። በተመሳሳይ በሜዳቸው በኢትዮጵያ ቡና ከተረቱበት ቡድን የአንድ ተጨዋች ቅያሪ ያደረጉት ድሬደዋዎች ከፊት የኩዋሜ አትራም ተጣማሪ የነበረውን ዳኛቸው በቀለን በያሬድ ዘውድነህ በመተካት ኩዋሜን ከፊት ለብቻው በነጠቀም በ4-1-4-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ምንተስኖት አዳነ ከበሀይሉ አሰፋ ተቀብሎ ከርቀት በሞከረው እና ወደ ውጪ በወጣው ኳስ የተነቃቃ መስሎ የጀመረው ጨዋታ ሁለተኛ ሙከራ ለመመልከት በርካታ ደቂቃዎችን ያስጠበቀ ፈዛዛ እንቅስቃሴን ነበር ያስከተለው። በተመሳሳይ መልኩ ኳስ መስርተው ከሜዳቸው ለመውጣት ጥረት የሚያደርጉት ሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ ፍጥነታቸው ዝግ ማለት ተጋጣሚ የመከላከል ቅርፁን እንዲይዝ ጊዜ የሚሰጥ አይነት በመሆኑ ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትኑ ተከታታይ ሙከራዎችን ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በሜዳው ቁመት በተጨዋቾቻቸው መሀል ይኖር የነበረው ሰፊ ርቀትም የቅብብሎቻቸውን ስኬት አውርዶት አብዛኛው እንቅስቃሴያቸው በመሀለኛው ሜዳ ላይ ያመዘነ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚረዱ የተሻሉ የሚባሉ ኳሶችን አልፎ አልፎ ሲጥሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ከምንተስኖት የ1ኛ ደቂቃ ሙከራ በኃላ 23ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ባሻገረው ኳስ ጥሩ አጋጣሚን ቢፈጥሩም ጀማል ጣሰው ከአቡበከር ሳኒ እና ምንተስኖት አዳነ ጋር ታግሎ አድኖባቸዋል። ከሶስት ደቂቃ በኃላ ደግሞ እስከ ሀያኛው ደቂቃ ድረስ ከነበረበት የግራ መስመር አጥቂነት ወደቀኝ የዞረው ጋዲሳ መብራቴ ከዛው ከቀኝ መስመር ወደ ጎን በመሄድ በሳጥን ውስጥ ጥሩ አጋጣሚ ቢፈጥርም የተጠቀመበት አልነበረም። 

ባለፈው ሳምንት ቅድስ ጊዮርጊስን ከረታው የወላይታ ድቻ ቡድን ጋር ተመሳሳይ ቅርፅ እና አቀራረብ የነበራቸው ድሬደዋዎች አንድም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ቢቆዩም 28ኛው ደቂቃ ላይ ኩዋሜ አትራም በግምት ከሰላሳ ሜትር በቀጥታ በመምታት ባስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ በኃላም ቢሆን ብርቱካናማዎቹ ያደረጉት ብቸኛ ሙከራ 34ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ኢሳያስ ከርቀት መቶ ሮበርት በቀላሉ ያዳነበትን ኳስ ነበር። በዚህ ሁኔታ በተቀዛቀዘ መንፈስ የተጠናቀቀው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የተጨዋቾች ጉዳት እና የዳኛ ፊሽካ የታጀበ ነበር። ጨዋታው አብቅቶ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ካመሩ በኃላ በካታንጋ እና ሚስማር ተራ በተቀመጡ ደጋፊዎች መሀል የተፈጠረው ግጭት እና ድንጋይ መወራወር ደግሞ ሌላ የሚስከፋ የእለቱ ክስተት ሆኗል። የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት ርምጃም በደጋፊዎቹ መሀል ሰፊ ክፍተት እንዲኖር በማድረግ ግጭቱ እንዳይባባስ አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ቀኝ መስመር ባደላ መልኩ አብዱልከሪም መሀመድን ወደፊት በመግፋት በታሻጋሪ ኳሶች በማጥቃት የጀመሩ ሲሆን ከመጀመሪያው በተሻለ አስፈሪነትን ተላብሰው ታይተዋል። በአንፃሩ ድሬደዋዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ኃላ አፈግፍገው የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቀነስ የሞከሩ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ ዕድሎችም ወደ ጎል የቀረቡባቸው ጊዜዎች ነበሩ። ከነዚህ መሀል ምንም እንኳን ወደ ሙከራነት ባይቀየርም 50ኛው ደቂቃ ላይ ኩዋሜ አትራም ከዮሴፍ ደሙዬ ሳጥን ውስጥ ሆኖ የተቀበለው ኳስ ተጠቃሽ ነው። 

በዚህ መልኩ የቀጠለው ጨዋታ 61ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስተናግዷል። ጎሉ የኩዋሜ የቅጣት ምት ከተቆጠረበት አካባቢ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አበባው ቡታቆ በተመሳሳይ መልኩ በቀጥታ በመምታት ያስቆጠረው ሌላ ቅጣት ምት ነበር። ከግቡ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች እጅግ ተጋግሎ በቀጠለው ጨዋታ ድንገተኛ ጥቃት የከፈቱት ድሬዎች አጥቂያቸው ኩዋሜ አትራም በቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን አካባቢ ወድቆ የቅጣት ምት ሳይሰጠው በመቅረቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በዚህ አጋጣሚም በአበባው ቅጣት ምት አግባብነት ደስተኛ ያልነበሩት አሰልጣኝ ስምኦን አባይ ለኩዋሜ ቅጣት ካለመሰጠቱ ጋር ተዳምሮ ከዳኛው ጋር በፈጠሩት አለመግባባት በቀይ ካርድ ለመውጣት ተገደዋል። የጨዋታው ጊዚያዊ ግለትም እየበረደ ሃዶ መጀመሪያ የነበረውን መልክ ይዟል። 

የመጨረሻዎቹን ሰላሳ ደቂቃዎች አዳነ ግርማን እና ኢብራሂማ ፎፋናን ቀይረው በማስገባት በተቻላቸው መጠን ኳሶችን ወደፊት በመላክ ጎል ለማግኘት ሲሞክሩ ያመሹት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 68ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥን ውጪ በመታት ኳስ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ በጭማሪ ደቂቃ ከአበባው ብታቆ የተነሳውን ቅጣት ምት አዳነ ግርማ በግንባር የሞከረበትም አጋጣሚም ቡድኑ ለግብ የቀረበበት ነበር። ወደ መጠንቀቁ ያመዘኑት ድሬደዎች ደግሞ በአናጋው ባድግ እና ዘላለም ኢሳያስ ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም በተለይ 84ኛው ደቂቃ ላይ ሳውሪል ኦልሪሽን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ሙሉ ትኩረታቸው ውጤት ማስጠበቁ ላይ ሆኖ ታይቷል። በዚህም ተሳክቶላቸው ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው በጣም ፍትጊያ የበዛበት እና ከመጀመሪያው ሀይል የተቀላቀለበት ነበር። ማሸነፍ ፈልገን ነበር። በፈለግነው መልኩ የጎል ዕድሎች አልፈጠርንም። እኩል ለእኩል መውጣታችን ደስ የሚል አይደለም። ዛሬ የምንፈልገውን ያህል ተጫውተናል ማለት አይቻልም። በተለይ በማጥቃቱ በኩል በጣም ደካሞች ነበርን። ቀላል የሆኑ ኳሶች እንሳሳት ነበር። በቀጣይ ጨዋታዎች እንደዚህን ችግሮቻችንን አርመን እንቀርባለን።

አሰልጣኝ ስምዖን አባይ – ድሬደዋ ከተማ

ከጨዋታው ውጤት ይዘን ለመመለስ ነበር የመጣነው። በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለው። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነው የሞከርነው። ያን ያደረግንበት ምክንያትም በተከታታይ ካስመዘገብነው ደካማ ውጤት አንፃር ነው። በዚህ ሁኔታ ጊዮርጊስን ከመሰለ ቡድን ጋር ስንጫወት መጠንቀቅ እና ነገሮችን በእርጋታ ማየት ነበረብን። ልጆቼም ይህን ነገር በሚገባ ተግብረውታል ብዬ አስባለው።

ዳኛው እኔን በቀይ ማስወጣቱ ተገቢ ነበር። ሊያልፈኝ ይችል ነበረ ቢሆንም ስሜታዊ ሆኜ ነበር። ቡድኔ ካለበት ሁኔታ አንፃር እንጂ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት የዲሲፕሊን ችግር አሳይቼ አላውቅም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *