ሪፖርት | መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የአዲስ አበባ ስታድየም ባስተናገደው የዕለቱ የ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መከላከያ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደ ሲሆን በውጤቱም 0-0 ተለያይተዋል።

ከአስራአምስት ቀናት በፊት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር 1-1 ከተለያየው ስብስባቸው የአምስት ተጨዋቾች ለውጥ ያደረጉት መከላከያዎች ቴውድሮስ በቀለን ፣ አማኑኤል ተሾመን ፣ ቴውድሮስ ታፈሰን ፣ አቤል ከበደን እና ማራኪ ወርቁን በሙሉቀን ደሳለኝ ፣ ሳሙኤል ታዬ ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና አቅሌሲያስ ግርማ ተክተዋል። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ከመቐለው ሽንፈት በተደረገው ብቸኛ ቅያሪ ወንድሜነህ አይናለም ወደ ተጠባቂነት ወርዶ በምትኩ አምሀ በለጠ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቷል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉፉክር በተመለከትንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መከላከያዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ጨዋታው አስረኛው ደቂቃ ላይ እስኪደርስም ምንይሉ ወንድሙ ከቅጣት ምት እንዲሁም የመስመር ተከላካዮቹ ሽመልስ ተገኝ እና ታፈሰ ሰረካ ከሳጥን ውጪ የሞከሯቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስፍን ኪዳኔ በተሰነጠቀለት ኳስ ከ አበበ ጋር እየታገለ መሳይ አያኖ ጋር ደርሶ የሳተው ኳስ ግን ከሁሉም በላይ ቡድኑ ለጎል የቀረበበት ነበር። ይህ የመከላከያዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ግን በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ሊታይ አልቻለም። ቡድኑ ቀጣዩን ሙከራ እንኳን ያደረገው 41ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከረዥም ርቀት ወደጎል በላከው እና በግቡ ቋሚ በተመለሰው የቅጣት ምት ኳስ ነበር። 

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ሲዳማዎች መሀል ሜዳ ላይ ተጋጣሚያቸው ሊቀባበል የሚሞክረውን ኳስ ጫና ፈጥሮ በመንጠቁ በኩል የተዋጣላቸው ሆነዋል። በዚህ አኳኃን ከሚያገኟቸው ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስም አልተቸገሩም። በተለይ ተጋጣሚያቸው መሀል ሜዳውን ካለፈ በኃላ የሚነጠቁትን ኳሶች በአግባቡ በማሰራጨቱ በኩል የዮሴፍ ዮሀንስ ሚና በግልፅ ተደጋግሞ ታይቷል። ተጨዋቹ በመከላከያዎች የመስመር እና የመሀል ተከላካዮች መሀል መሬት ለመሬት ይልካቸው ከነበሩ ኳሶች መነሻነትም ሲዳማዎች በክፍሉ ኬአ ፣ ሀብታሙ ገዛሀን እና ትርታዬ ደመቀ አማካይነት አደጋ ያላቸውን ኳሶች ወደ ውስጥ መጣል ችለው ነበር። ከዚህ ውጪ ቡድኑ 15ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ገዛሀኝ ከርቀት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ ላይ በአዲስ ግደይ ቅጣት ምት ጥሩ ሙከራዎችን ቢያደርግም በእጅጉ ለጎል የቀተበበት አጋጣሚ የተፈጠረው ግን በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚህም ከግራ መስመር የተጣለውን ኳስ አቤል ማሞ ማራቅ ሳይችል ቀርቶ አዲስ ግደይ ከግቡ አፋፍ ላይ ግልፅ የማግባት ዕድል ቢያገኝም ሙከራው ለማመን በሚከብድ መልኩ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ከእረፍት መልስ በነበሩት የመጀመሪያ ደቂቃዎችም የሲዳማ ቡናዎች የሙከራ የበላይነት ቀጥሎ ታይቷል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ ከቀኝ መስመር ከላከው ኳስ አዲስ ግደይ እና ባዬ ገዛሀኝ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም በአቤል ማሞ ጥረት ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። አቤል የ55ኛው ደቂቃ የባዬ ገዛሀኝን ድንቅ ቅጣት ምትም ማዳን ችሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ከአዲስ ግደይ እና አምሀ በለጠ ጥምረት የተገኘውን ኳስ ሀብታሙ ገዛሀኝ ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል። ሲዳማዎች በሚያጠቁበት ወቅት የቀኝ መስመር አጥቂነቱን ቦታ ለትርታዬ በመተው ሶስቱን አጥቂዎቻቸውን አዲስ ፣ ባዬ እና ሀብታሙን በሳጥን ውስጥ እንዲጠብቁ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተደጋግሞ ይታይ ነበር። ይህ ዕቅድ መሀል ሜዳ ላይ አምሀ በለጠን እና ዮሴፍ ዮሀንስን የሚያጋልጥ የነበረ እና ለመከላከያዎች የኳስ ፍሰት የተመቸ ቢሆንም የጦሩ የአማካይ ክፍል ከበሀይሉ ግርማ ፊት በነበረው የሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና መስፍን ኪዳኔ ሶስት የመስመር አማካዮች ጥምረት ተመሳሳይ የአጨዋወት ባህሪ ምክንያት የተጋጣሚያቸውን ደካማ ጎን መጠቀም አልቻሉም። ሆኖም 57ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ ከበሀይሉ ጎን በመሆን የተሻለ ጥቃትን የማስጀመር ሀላፊነትን ለመወጣት ሞክሯል። 

ከቅያሪው በኃላ የሲዳማዎች ሙከራ ጋብ ያለ ሲሆን እንግዶቹ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በአዲስ እና ሀብታሙ አማካይነት ሁለት ተጨማሪ ሙከራዎችን ብቻ ነበር ያደረጉት። በአንፃሩ እየተሻሻሉ የመጡት መከላከያዎች ደግሞ ጨዋታውን ጨርሰው መውጣት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል። በተለይ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከበሀይሉ እና መስፍን ኪዳኔ ቅንጅት ሳጥን ውስጥ ሳሙኤል ሳሊሶ ያገኘው ዕድል ወደ ግብ ሙከራነት ሳይቀየር መቅረቱ ለቡድኑ በጣሙን የሚያስቆጭ ነበር። ከዚህ ውጪ 80ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው እንዲሁም ተቀይሮ የገባው የተሻ ግዛው በጭማሪ ደቂቃዎች ሁለት ጊዜ የሞከራቸው ኳሶች ለጦሩ የመጨረሻ ደቂቃ የበላይነት ማሳያ ነበሩ። ሆኖም ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታው ያለግብ ከመጠናቀቅ አልዳነም። ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሲዳማ ቡና በነበረበት የ8ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ – መከላከያ

ከነበረብን እንቅስቃሴ አንፃር አንድ ነጥብ ያንሳል። አሸንፈን መውጣት ነበረብን። ከእረፍት በፊት እና በኃላ ያገኘናቸው አራት እና አምስት የሚሆኑ አጋጣሚዎች ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ነበሩ። ኳስ የሚጫወት ቡድን ነው። ሳጥን ውስጥ እንገባለን ።ግን የመጨረስ ችግር አለብን። ሰው ላይ የሚሰራ ነገር በአንዴ የሚሰራ አይደለም። ጊዜ ይፈልጋል። ድግግሞሽንም ይጠይቃል እንደየአቀባበሉ ማለት ነው። ዋናው ነገር ግን ጎል ላይ ከደረስን በኃላ እርጋታ የሚያስፈልገን መሆኑ ነው። ጊዜ ቢፈጅም ይህን ችግራችንን እናሻሽላለን።

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ ጨዋታ ነበር። ብዙም ውበት አልነበረውም። እኛም ተጋጣሚ ሲጫወት ብዙ የማየት ዕድል ስላልነበረን ጥንቃቄን መርጠን አጨዋወቱን ለማየት በማሰብ በመልሶ ማጥቃት ተጫውተናል።  በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ወደ መጨረሻው ላይ ጫና ፈጥረውብን ነበር። በዛም ሰዐት ተጠንቅቀን ተጫውተናል። ከዛ ውጪ የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ የነበሩ ኳሶችን በመፍቀድ ጫና አሳድሮብን ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *