የአአ ከተማ ዋንጫ የሽልማት መርሀ-ግብር ነገ ይካሄዳል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነገ ማምሻውን በጁፒተር ሆቴል 12ኛው የአአ ሲቲ ከተማ ዋንጫ ላይ ለተሳተፉ አካላት እና ክለቦች እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶች የምስጋና እና የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ-ግብር ያካሄዳል ።

ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 በድምቀት ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ  ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ውድድሮች ሁሉ በብዙ መለኪያ የተሻለ እንደነበር ተመስክሮለታል። በየጨዋታዎቹ በነበረው ፉክክር ፣ ውድድሩን ሳቢ ለማድረግ በቀረቡ ሽልማቶች ፣ በርካታ ተመልካች የተከታተለው በመሆኑ እና  ከስፖንሰር እና ከተመልካች ከፍተኛ ገቢ የተገኘበት እንደሆነም ይታወሳል ።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለውድድሩ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል ያላቸው አካላት የምስጋና እና የዕውቅና አሰጣጥ መርሀ-ግብር ነገ ማምሻውን በ11:00 ላይ በጁፒተር ሆቴል ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶች ፊት ያካሄዳል። መርሀ-ግብሩን አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ አቃቢ ነዋይ የሆኑት ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍስሀ ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት የዝግጅቱ ዋና አላማ ከሜዳ ገቢ (ከወጪ ቀሪ) ለክለቦች ክፍያ መፈፀም እና አሁን ይፋ የማይደረግ በዕለቱ የሚገለፅ ለተለያዩ አካላት ልዩ የማስታወሻ የክብር ሽልማት መስጠት ነው። በተጨማሪም በቀጣይ 13ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ እንዴት ለማዘጋጀት እንደታሰበ እቅድ ይቀርባል ብለውናል ።

በሽልማት ስነስርአቱ ላይ ከተገኘው የሜዳ ገቢ ውድድሩን በቀዳሚነት ላጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 መቶ ሺህ ብር እንደሚበረከትና ሌሎቹ ክለቦችም እንደየደረጃቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚበረከትላቸው ሰምተናል። ይህም በአአ ከተማ ዋንጫ የ12 አመታት ታሪክ ከፍተኛው ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *