አል ሰላም ዋኡ ቡድን አባላት እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም

የደቡብ ሱዳኑ አል ሰላም ዋኡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ላለበት ጨዋታ ወደ ኢትዮጵያ እስካሁን አለመምጣቱ ታውቋል። እሁድ ከሚደረገው ጨዋታ አስቀድሞም የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ናይጄሪያዊው ተከላካይ ካሉ ሚካኤል ከክለቡ መልቀቂያ እንዲሰጠው መጠየቁን ተከትሎ በችግሮች ውስጥ ሆኖ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ካሉ በዋኡ የሁለት ዓመት ከስምንት ወር ቆይታ ያደረገ ሲሆን ከክለቡ ጋር ለመለያየት መወሰኑን ተከትሎ አል ሰላም ዋኡ ተጫዋቹን ለማቆየት ጥረት ማድረግ ጀምሯል፡፡ ክለቡ አርብ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገልፆ የነበረ ቢሆንም ሶከር ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ባገኘችው መረጃ መሰረት ክለቡ ወደ አዲስ አበባ አልመጣም፡፡ ቅዳሜ የቡድኑ ልኡካን ይደርሳሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዳሜ ይመጣሉ ከመባሉ ውጪ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበትን ሰዓት አለማወቁን ተነግሯል፡፡ አል ሰላም ባሳለፍነው ሳምንት በዋኡ ከተማ የነበረውን ዝግጅት አጠናቅቆ ወደ ጁባ በመጓዝ ዝግጅቱን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ልክእንደ አል ሰላም ዋኡ ሁሉ ሌላኛው የደቡብ ሱዳን ክለብ የሆነው አል ሂላል ጁባ ከቱኒዚያው ዩኒየን ስፖርቲቭ ደ ቤን ጎርዳን ጋር በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ስፍራው በግዜው ባለመጓዙ ጨዋታው እንዲራዘምለት ለካፍ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ በተለያዩ ግዜያት በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ክለቦች በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ እና የአየር ላይ ጉዞ ለማድረግ ሲሳናቸው እና ጨዋታዎች ሲራዘሙ እና በፎርፎ ሲጠናቀቁ የተመዱ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *