“ቻምፒየንስ ሊጉ ከፕሪምየር ሊጉ ይለያል” ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ

የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች መደረግ ጀምረዋል። በውድድሩ ላይ ለተከታታይ አራተኛ አመት የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ እሁድ የደቡብ ሱዳኑ አል ሰላም ዋኡን አዲስ አበባ ላይ ያስተናግዳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና በተመሳሳይ ውድድር ወደ ምድብ ማለፈ የቻለ ሲሆን ፓርቹጋላዊው አሰልጣኝ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ ስለቡድናቸው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለተጋጣሚያቸው እና ጨዋታው የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ስለቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮው አቋም

በዚህ ላይ የተለየ ሃሳብ አለኝ፡፡ ከዓምናው ጋር ሲነፃፃር ቡድናችን አንድ ነጥብ ብቻ ነው ዝቅ ያለው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ 7ቱን በሜዳው እና 5ቱን ከሜዳው ውጪ ነበር፡፡ በአሁን የውድድር ዘመን 6 በሜዳችን እንዲሁም 6 ከሜዳችን ውጪ ነው የተጫወትነው፡፡ አምና ክለቡ ካደረገው አምስት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች መካከል 3ቱን ከአዲስ አበባ ውጪ ነበር፡፡ ከዓምናው ዘንድሮ የተሻልን ነን የሚል ሃሳብ አለኝ ምክንያቱም ከአዲስ አበባ ውጪ ቡዙ ጨዋታዎችን አድርገናል፡፡ የቡድን ጥልቀትን ከተመለከትን የበዛ የተጫዋች ጉዳት አጋጥሞናል፡፡ ብዙ ተጫዋቾች ለብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ከእኛ ጋር ለተወሰነ ግዜ አልነበሩም፡፡ እነዚህ ነገሮች የውድድር አመቱን ለመጀመር ትንሽ አስቸግረውናል፡፡ አሁን ቡድናችን ጥሩ ነው ምክንያቱም የተወሰኑ ተጫዋቾች ከጉዳት እየተመለሱልን ናቸው፡፡ በዚህም ደስተኛ ነን፡፡ ቻምፒየንስ ሊጉ ከፕሪምየር ሊጉ ይለያል፡፡ ድባቡ የተለየ ነው እንዲሁም ለጨዋታው የሚሰጠው ግምትም የተለየ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዚህ ውድድር ዝግጁ ነው፡፡

ስለአል ሰላም ዋኡ

በጣም ትንሽ መረጃ ነው ስለተጋጣሚያችን ያለን፡፡ ዓምና በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምን እንዳደረጉ እናውቃለን፡፡ በሊግ ላይ ስላላቸው አቋም ግን መረጃዎችን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም ለማግኘት ጥረት አድርገን አልተሳካልንም፡፡ ስለቡድኑ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ዋናው ቁም ነገር በቡድናችን ላይ እና ሃሳባችን ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኃላ ተጋጣሚያችንን በሚገባ እናውቀዋለን ስለዚህም ለመልሱ ጨዋታ በሚገባ እንዘጋጃለን፡፡

ኳስን ይዞ የሚጫወት ቡድን ስለመገንባት

አንድ ቡድን ግብ ለማስቆጠር ኳስ ታስፈልገዋለች፡፡ ኳሱ አንተ ጋር ከሌለ ግብ ማስቆጠር አትችልም፡፡ ኳስ አንተ ጋር ብዙ ግዜ የምትገኝ ከሆነ ግብ የማስቆጠር እና ወደ ግብ የመቅረብ እድልህ ከፍ ይላል፡፡ ሁሌም ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር ነው ጥረታችን፡፡ በሊግ ጨዋታዎች በአብዛኛው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበረን፡፡ ሆኖም ግብ ማስቆጠር ይገባናል፡፡ ባለፉት ግዜያት ግብ ማስቆጠር የሚችል አጥቂ አልነበረንም፡፡ አሁን ላይ ነገሮች ጥሩ ናቸው፡፡ ለመሻሻል እና ጨዋታችን ለማስተካከልም እየሞከርን ነው፡፡

ተጫዋቾቼ የቡድኑን አጨዋወት በሚገባ እየተላመዱት ነው፡፡ የውድድር አመቱ ሲጀመር ሁለት ዋንጫዎችን አሸንፈናል፡፡ በሊጉ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግብ ተቆጥሮብናል ከዛ በፊት ግን ግባችንን በለማስደፈርም ጥሩ ነበረን፡፡ ይህ ለውጥ ነው እናም ተጫዋቾቼ ሃሳባችንን እየተረዱ እንደመጡ መናገር ይቻላል፡፡

በቻምፒየንስ ሊጉ ሩቅ መጓዝ

አዎ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ ግን ከፊታችን ስላለው የደርሶ መልስ ጨዋታ ነው ማሰብ የሚገባን፡፡ ከእዛ በኃላ ነው ስለሌላኛው ጨዋታ ማሰብ የምንጀምረው፡፡ አሁን ላይ የደቡብ ሱዳኑን ክለብ ከውድደር ማሰወጣት ነው አላማችን፡፡ በቀጣይ ስላሉት ጨዋታዎች ለማሰብ የአሁንን ጨዋታ ማሸነፍ አለብን፡፡

ሁል ግዜም ለተጫዋቼ የምነግራቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ተጫዋች የለውም ግን ያሉት የምርጦች ምርጥ ተጫዋቾች መያዙን ነው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ደግሞ ይህንን ማስመከር አለባቸው፡፡ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ መነሳሳት ከሌለ የምርጦች ምርጥ የሚለው ነገር እዚህ ላይ አይሰራም፡፡ አዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾች አሉን ይህም ለመነሳሳቱ አዲስ አቅም ነው የሚሆነው፡፡

በጉዳት ላይ ስለሚገኙ ተጫዋቾች

አንዳንድ ግዜ መጠነኛ ጉዳት ላይ ተጫዋቾች እረፈት ይፈልጋሉ፡፡ ሮበርት ከጨዋታው ውጪ ነው አይደለም የሚለውን ቅዳሜ ከምናደርገው ልምምድ በኃላ ነው የምንወስነው፡፡ ስለዚህም ከልምምዱ በኃላ ሁሉንም ነገር እናያለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *