​የ12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመዝጊያ እና የሽልማት ፕሮግራም ተከናወነ

ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 8 ድረስ በተካሄደው 12ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድር ላይ ለተሳተፉ ክለቦች እና ለውድድሩ ድምቀት አስተዋጸኦ ላደረጉ አካላት የገንዘብ እና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቷል። ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በተከናወነው ዝግጅት በውድድሩ ላይ የተካፈሉ የክለብ ተወካዮች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሚዲያ አባላት ባሉበት የእውቅና መስጠት ፕሮግራም የተደረገ ሲሆን ለ13ኛ ጊዜ ስለሚካሄደውም የአዲስ አበባ ዋንጫ ቀጣይ እቅዶችም መጠነኛ ማብራሪዎች ተሰጥተውበታል።

ዝግጅቱ በስፍራው በተገኙት የክብር እንግዳ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የአዲስ አበባ መስተደድር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረ ሲሆን ሃላፊውም ያለፈው ውድድር ደማቅ እንደነበር አስታውሰው ለቀጣይ ከዚህ የተሻለ ውድድር ለማዘጋጀት ጥረቶች ከወዲሁ እንዲጀመሩ አሳስበዋል።

በመቀጠልም ስድስት የአዲስ አበባ ከተማ እና ሁለት ተጋባዥ የክልል ክለቦችን ባሳተፈው ውድድር ላይ ለነበሩ ክለቦች እንደየ ደረጃቸው የገንዘብ እና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ክለቦቹም በተወካዮቻቸው በኩል ሽልማታቸውን ወስደዋል። አንደኛ ለወጣው 15% ፣ ሁለተኛ ለወጣው 10% ፣ ሶስተኛ ለወጣው 4% እንዲሁም ከ4 -6 ለወጡ ክለቦች 3% ፌደሬሽኑ ከውድድሩ የስታዲየም ገቢ ከወጪ ቀሪ ካገኘው ገቢ በመቶኛ በማስላት ለየክለቦቹ መስጠቱ የታወቀ ሲሆን ያገኙት የገንዘብ መጠንም እንደሚከተለው ይቀመጣል።

1ኛ ለወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ 500,304 ብር
2ኛ ለወጣው ኢትዮጰያ ቡና 433,536 ብር
3ኛ ለወጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 133,414.40 ብር
እንዲሁም ለቀሪዎቹ ሶስት ክለቦች 100,060.80 ብር ፌደሬሽኑ በሽልማት መልክ አበርክቷል።
በውድድሩ ደምብ መሰረት ተጋባዥ ክለቦች ከሚገኘው የስታዲየም ገቢ ምንም አይነት ክፍያ እንደማይፈፀምላቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህንን ደምብ ለማሻሻል በቀጣይ ፌደሬሽኑ ከክለቦች ጋር ተወያይቶ ለማሻሻል እንዳቀደ አስታውቋል።

ፌደሬሽኑ ለኢንተርናሽናል አልቢትር በአምላክ ተሰማ ፣ ለኢንተርናሽናል አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ ፣ ለአቶ ብርሃኑ ሃይሌ እንዲሁም ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ በልዩ ሁኔታ ለረጅም አመታት ለፌደሬሽኑ ባበረከቱት አስተዋጸኦ የማስታወሻ ሽልማት አበርክቷል። በአሁኑ ወቅት በህመም ላይ ለሚገኙት አሰልጣኝ ስዩም አባተ ፌደሬሽኑ የ10,000 ብር የመታከሚያ ገንዘብ ማበርከቱ የታወቀ ሲሆን ወንድማቸው አሰልጣኝ ሰለሞን አባተም በሽልማቱ እና በማስታወሻ ስጦታው መደሰታቸውን በመግለጽ ፌደሬሽኑን አመስግነዋል።ከነዚህ በተጨማሪ ለፀጥታ አካላት ፣ ለስፖንሰር አድርጊ ድርጅቶች እና ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲገባደድ ላደረጉ ግለሰቦች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በመጪው አመት ለ13ኛ ጊዜ የሚደረገውን የሲቲ ካፕ ውድድር ለማድመቅ እና ከዚህኛው አመት የተሻለ ለማድረግ ፌደሬሽኑ እንቅስቃሴዎችን ከወዲሁ መጀመሩ ያስታወቀ ሲሆን ሁለት ተጋባዥ የውጪ ሀገር ክለቦችን ለማምጣት እንዳሰበም ጨምሮ ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *