​ሪፖርት | ከታሰበው ሰአት ዘግይቶ የተጀመረው የአዳማ እና ጅማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በ15ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም አዳማ ከተማን ከጅማ አባጅፋር ያገናኘው የኦሮሚያ ደርቢ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በሳምንቱ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው በዛሬው የአዳማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊጉ እርስ በእረስ የተገናኙበት አጋጣሚ የሌለ ቢሆንም ለመጀመርያ ጊዜ በሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ካሉበት የነጥብ መቀራረብ እና ከሚከተሉት የማጥቃት አጨዋወት ባለፈ ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ መሆን ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።
አዳማ ከተማ ጥር 20 በሜዳው ወልዋሎን በጥሩ አቋም 3 ለምንም ሲረታ ከነበረው የቡድን ስብስብ ውስጥ ግብ ጠባቂውን ዳንኤል ተሾመን በጃኮ ፔንዛ መጠነኛ ጉዳት ባስተናገደው ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም ምትክ ሱሌማን መሀመድን በማሰለፍ ለዛሬው ጨዋታ ሲገቡ በአንፃሩ ጅማ አባጅፋር በአዲስ አበባ ስታዲዮም ጥር 23 የሊጉ መሪ ደደቢትን በመልካም እንቅስቃሴ 2 – 1 ሲያሸንፍ ከነበረው የቡድን ስብስብ ውስጥ በቅጣት ባጣው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ምትክ ብሩክ ተሾመን ፣ አማካዩ አሚን ነስሩን የመሀል ተከላካይ በማደረግ ቢንያም ሲራጅን በንጋቱ ገ/ሦላሴ ተክቶ ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።

ዘጠኝ ሰአት ሊደረግ መርሀግብር ተይዞለት በነበረው የዛሬው ጨዋታ መጀመር ከሚገባው ጊዜ 48 ደቂቃ መዘግየቱ ከጨዋታው መጀመር በፊት የነበረ አስገራሚ አጋጣሚ ነበር። ይሄን ያህል ደቂቃ ለመዘግየቱ  ምክንያት የሆነው ሁለት ነገሮች ሲሆኑ አንደኛው ምክንያት አስቀድሞ በቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ወቅት መጠናቀቅ የሚገባው ጉዳይ ሜዳ ላይ እንዲስተካከል መደረጉ ነው። የአዳማ ከተማ እና የጅማ አባጅፋር የእግር ካልሲ ተመሳሳይ ነጭ በመሆኑ ጨዋታውን ለማጫወት አስቸጋሪ ስለሆነ እንግዳው ቡድን ጅማ አባጅፋር እንዲቀይር ታዞ ካረፉበት ሆቴል ካልሲ እስኪመጣ ድረስ 34 ደቂቃ ዘግይቷል ። ይህ ድርጊት በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብ መሰረት ከሆነ 30 ደቂቃ በማለፉ ለአዳማ ከተማ ፎርፌ የሚያሰጠው ቢሆንም አዳማዎች ይህንን የህግ ጥሰትን ተጠቅመው ከጨዋታው ፎርፌ ለማግኘት ጥያቄ አላቀረቡም ። ሌላው ለተጨማሪ 14 ደቂቃ እንዲዘገይ ያደረገው ጉዳይ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ሀቢብ  እንዲሁም ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ እና ኢብራሂም ጀላን በክብር እንግድነት ተገኝተው ለህዝቡ የሚያስተላልፉት መልክት የወሰደው ጊዜ ነው ። በአጠቃላይ የዕለቱ ኮሚሽነር የሆኑት አቶ መኮንን አስረስ የጨዋታውን መርሀግብር ጊዜውን ጠብቆ እንዳይሄድ ያሳዩት ቸልተኝነት ለዛሬው ጨዋታ መዘግየት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮች በድጋሚ እንዳይፈጠሩ ትምህርት ሰቶ ማለፍ አለበት እንላለን።

በዛሬው እለት በክብር እንግድነት የተገኙት የአዳማ ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች ሀቢብ ለህዝቡ መልክት እያስተላለፉ ባለበት ወቅት የአዳማ ደጋፊዎች ድምፃቸው ከፍ በማድረግ በካታንጋ በኩል ያለው በጊዛዊነት ተሰርቶ ይነሳል ቢባልም  እስካሁን እያገለገለ የሚገኘውና በስጋት የሚታየው  ከእንጨት የተሰራ መቀመጫ ወንበር ይቀየር በማለት ለከንቲባዋ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን  ከንቲባዋም ጥያቄውን ተቀብለው እንደሚቀየር ገልፀዋል ።

ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ በመሩት በዛሬው ጨዋታ አመዛኙን የመጀመርያ አጋማሽ ያለ ጎል እረፍት ይውጡ እንጂ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መልካም  እንቅስቃሴ መመልከት ችለናል። በ7ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ከንአን ማርክነህ ቁመቱን ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በወጣበት አጋጣሚ አዳማ የጎል ሙከራ ቅድሚያውን ይዘዋል።
ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር ሁለቱም ቡድኖች በአመዛኙ መሀል የሜዳ ላይ ተገድበው መንቀሳቀሳቸው እንዲቀዘቅዝ አድርገታል። አዳማ የመስመር አጥቂዎቹ ሲሳይ ቶሌ እና በረከት ደስታን ቦታ በመቀያየር ለዳዋ ሆቴሳ የተሻሉ ኳሶች እንዲደርሱ ለማድረግ ቢሞክሩም እንዳሰቡት ሊሳካ አልቻለም። ጅማዎች ጥንቃቄን መሰረት ባደረገ አጨዋወታቸው ውስጥ ፈጣን በሆኑት አጥቂዎቻቸው ለመጠቀም ረጃጅም ኳሶች ወደ አዳማ የግብ ክልል ሲጥሉ ታይተዋል። በ21ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገብረኪዳን ከመስመር ወደ ሳጥን በመግባት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ኳስም የሚጠቀስ ነበር።
ጨዋታው የነበረውን ጥሩ እንቅስቃሴ ቀጥሎ እየሄደ ባለበት ሰአት የጨዋታውን መልክ የሚቀይሩ ሀይል ወደበዛበት አጨዋወት መግባታቸው እና በተጨዋቾች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ጨዋታውን ወደ  ውዝግቦች እንዲገባ አድርጎት ጨዋታው መቆራረጥ ቢበዛበትም የተሻሉ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል። በ33ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳው ቀኝ መስመር ለሳጥኑ በቀረበ ቦታ ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ መትቶ ዳንኤል አጄ ያወጣበት በአዳማ በኩል ሲጠቀስ በ42ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ኢሳይያስ በጥሩ ሁኔታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ሳምሶን ቆሊቻ ብቻውን ከጃኮ ፔንዜ ፊት ለፊት ተገናኝቶ አገባው ሲባል ኳሷ በእግሩ ስር ሾልካ የሳተው ኳስ በጅማ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አሚን ነስሩ እና ዳንኤል አጄ ሳይግባቡ ሲጠባበቁ በፍጥነት በመሀል ሾልኮ ሲሳይ ቶሌ መትቶ መሬት ለመሬት ኳሷ ወጥታለች።
ሁለተኛው አጋማሽ የተለያዩ ክስተቶች ተስተናግደውበት አልፏል። በ48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ለጎሉ አምስት ሜትር ቅርበት ላይ ራሱ ተጠቅሞ ጎል ሊያስቆጥር የሚችልበትን አጋጣሚ  ለቡልቻ ሹራ ለቆለት ዳንኤል አጄ በአስገራሚ ሁኔታ ያዳነበት እንዲሁም በ50ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከ25 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት መቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ የወጣው ኳስ የማይታመን ነበር።

በሁለት ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ የቻሉት አዳማዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ በባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ጥምረት እያሳዩ ያሉት ከንአን ማርክነህ እና ዳዋ ሆቴሳ  በጥሩ ሁኔታ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ሳጥን ሰብረው በመግባት ከነአን ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄ ሲያወጣው ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ጎሉ ለዳዋ በውድድር አመቱ ያስመዘገበው 7ኛ ጎል ነው።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ የአቻነት ጎል ፍለጋ መጫን የጀመሩት ጅማዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ዮናስ ገረመው ያሻማውን ይሁን እንደሻው  በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግሩም ጎል በፍጥነት አቻ መሆን ችለዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው በጥሩ እይታ ከቀኝ መስመር አሻግሮለት ሄኖክ ኢሳያስ ብቻውን አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ሙከራ ጅማዎች መምራት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበረች።

ጅማዎች የአቻ ውጤትን ለማስጠበቅ ሲከላከሉ የታዩ ሲሆን 85ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ ግልፅ ጥፈት ሲሰራ የነበረው ሲሶኮ አዳማ ጥፋት በመፈፀሙ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ውሳኔውን በመቃወም ያሳየው ያልተገባ ባህሪ መታረም የሚገባው ሲሆን ምንአልባት የዕለቱ ኮሚሽነር የሚያቀርቡት ሪፖርት ጠንከር ካለ ሌላ ተጨማሪ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። በመጨረሻው ደቂቃ አዳማን ሦስት ነጥብ ሊያስገኝ የሚያስችለው አጋጣሚ 90ኛው ደቂቃ ላይ አንዳርጋቸው ይላቅ ያሻገረውን ከነአን ማርክነህ ከጎሉ በቅርብ ርቀት በግንባሩ መቶ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ በአስደናቂ ሁኔታ ይዞት ጨዋታው 1 – 1 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *