​ሪፖርት | ፋሲል ከተማ አርባምንጭን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት አጼ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ በተደረገ ጨዋታ ፋሲል ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

ፋሲል ከተማ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያውያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው ራምኬል ምተረክ ናትናኤል ጋንቹላን በመጀመርያ አሰላለፍ ሲያካትት ያሬድ ባየህ ከረጅም ጊዜ ጉዳት ተመልሶ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጧል። በተካከታታይ ጨዋታዎች የመጀመርያ አሰላለፉን ሳይቀይር እየተጠቀመ ያለው አርባምንጭ ከተማ በዚህም ሳምንት በቡድኑ ስብስበ ላይ ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በእንቅስቃሴ እና ወደግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ፋሲሎች በ4ኛ እና በ10ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም እና መሐሙድ ናስር አማካኝነት የአርባምንጭ የተከላካይ መስመርን መፈተን ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ 12ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ ናስር ከኤፍሬም የተሻገረለትን ኳስ ከግራ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ወደ ውስጥ በመግባት ወደግብነት ቀይሮት ፋሲልን ቀዳሚ አድርጓል። ከጅማ አባቡና ፋሲልን ዘንድሮ የተቀላቀለው መሐመድ በቅርብ ሳምንታት ያገኘውን የተሰላፊነት እድል በአግባቡ እየተጠቀመበት ይገኛል።

አርባምንጮች ከጎሉ በኋላ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም የጎል እድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ደክመው ታይተዋል። በ33ኛው ደቂቃ ተካልኝ ደጀኔ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራም በመጀመርያው አጋማሽ ቡድኑ የፈጠረው በነኛ የጎል እድል ነበር ። በፋሲል በኩል በ28ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ሲወጣ ናትናኤል ከሔኖክ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የመታውን ፅዮን መርዕድ ያመከነበት የሚጠቀሱ የጎል ሙከራዎች ናቸው።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የአሰላለፍ ለውጦች የነበሩ ሲሆን በተለይ አርባምንጮች አለልኝ አዘነን አስወጥተው አስጨናቂ ፀጋዬን በማስገባትና  የተከላካይ አማካይ ቁጥር በመቀነስ ወደፊት ተጭነው መጫወት ችለዋል። ሆኖም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የጎል እድል ሳይፈጥሩና ውጤቱን ለማስጠበቅ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀውን የፋሲል የተከላካይ ክፍል ሰብረው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይልቁንም ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ መምረጣቸው የካርዶች ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። 4 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ከመመልከታቸው በተጨማሪ አንድነት አዳነ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ በፈፀመው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል።
ጨዋታው በፋሲል አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አጼዎቹ ነጥባቸውን 22 በማድረስ የመጀመርያውን ዙር ሲያገባዱ በእዮብ ማለ አሰልጣኝነት ስር የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጮች በ13 ነጥብ ደረጃቸው ወደ 13ኛ ዝቅ ብሏል።


የአሠልጣኞች አስተያየት
ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ
” በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻልን ስለነበርን ጎል ማስቆጠር ችለናል። በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መከላከል ላይ አመዝነን ነበር። ጨዋታ በውጤት የተደገፈ ካልሆነ ለተጨዋቾቹ ሆነ ለደጋፊዎቻቸው ጥሩ ባለመሆኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ማጥቃት መሰረት አድርገን ነበር ስንጫወት የነበረው። ከ75 ደቂቃ በኋላ ግን ውጤቱ ስለሚያስፈልገን  ይበልጥ መከላከል መርጠናል።
” በመጀመሪያው ዙር ያሰብነውን ያህል ነጥብ አላገኝንም። እንደ ስራችን እና እንደ ስብስባችን ይሄ ውጤት አይገባንም ነበር። የተጨዋቾች ቅጣት እና ጉዳት ለዚህ ምክንያት ነው።  ለቀጣይ የተሻልን ሆነን እንቀርባለን። ”

ምክትል አሰልጣኝ ማትያስ ለማ – አርባምንጭ ከተማ
” የጨዋታውን ውጤት የቀየሩት ደጋፊዎች እና ዳኛው ናቸው። ዳኛው ቶሎ ቶሎ ስለሚያቆርጠዉ እኛ መጫወት አልቻልንም። በተደጋጋሚ ሰአት ሲያባክኑ እና ጨዋታው ሲቋረጥ ካርድ አላሳየም።
” ፋሲል ጥሩ ተጫውቷል። ግን ከኛ በልጦ አይደለም ፤ እኛ የተሻልን ነበርን። ሁለተኛው 45 ላይ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገን ነበር። ሁለት የተከላካይ አማካይ የነበረውን አንድ አድርገን ተጭነን መጫወት ችለን ነበር። ጎል ማግባት ግን አልቻልም። ለቀጣይ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *