​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ቡራዩ በድንቅ ግስጋሴው ሲቀጥል አአ ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

በዛ ያለ ተስተካካይ ጨዋታ ያለበት የዚህ ምድብ በዚህ ሳምንትም ሁለት ጨዋታዋች ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ጨዋታዋች በወጣላቸው መርሃ ግብር ተከናውነዋል፡፡

ከተከታታይ ሽንፈት በኃላ ወደ ድል የተመለሰው አዲስ አበባ ከተማ ደሴ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የቡድኑ ቋሚ አጥቂ ፍቃዱ ዓለሙ ባልተሰለፈበት ጨዋታ አአ ከተማ ከዕረፍት መልስ እንዳለማው ታደሰ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አሸንፎ በመውጣት መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።

ሰበታ ከተማ በሜዳው ነቀምት ከተማን አስተናግዶ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ከሽንፈት ተርፏል። በ23 ኛው ደቂቃ ላይ ክብረዓብ ፍሬው ነቀምት ከተማን ቀዳሚ አድርጎ የመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድረስ መሪነታቸውን ማስጠበቅ ቢችሉም የማታ ማታ አብይ ቡልቲ ቡድኑን ከሽንፈት ማዳን የቻለበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ወደ ያያ ቪሊጅ ያመራው ባህርዳር ከተማ ድል ቀንቶታል፡፡ ከኢኮስኮ ጨዋታውን ያደረገው ባህርዳር ከተማ በ5ኛው ደቂቃ ዳንኤል ኃይሉ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ላይ በኢኮስኮ ተጨዋች ሚኪያስ ፍቅሬ በተሰራበት ጥፋት እግሩ ላይ የስብራት አደጋ የደረሰበት ሲሆን ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጦም ነበር። ሚኪያስ በአሁኑ ሰዓት በዳን ሆስፒታል የሚገኝ ሲሆን በእግሩ ሶስት ቦታዋች ላይ ስብራት እደደረሰበት የቡድን መሪው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ወደ አክሱም ያቀናው ቡራዩ ከተማ በአስደናቂ ጉዞው በመቀጠል ድል አስመዝግቦ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። በ2ኛው እና በ24ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ደምሴ እና ኢሳያስ ታደሰ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ቡራዩ ቀዳሚ ሲሆኑ አክሱሞች ከዕረፍት መልስ ከመሸነፍ ያላደናቸውን ግብ በክፍሎም ሀብቶም አማካኝነት አስቆጥረዋል፡፡

ባህርዳር ላይ ፌዴራል ፖሊስን ያስተናገደው አውስኮድ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ተከታታይ ድል አሳክቷል። ሰለሞን ጌድዮን ፣ ተስሎች ሳይመን እና ሚኪያስ አለማየሁ የባህርዳሩን ክለብ ጎሎች አስቆጥረዋል። በጨዋታው ከፍተኛ ጉዳቶች የተስተናገዱ ሲሆን መልካሙ ዶል እና መስፍን ጎሳዬ ወደ ህክምና በመጓዝ ጭንቅላታቸው ላይ ሰፌት ሲደረግላቸው አቤል ደግሞ የጡንቻ መሰንጠቅ አግጥሞት ከሜዳ ወጥቷል።

መድን ሜዳ ላይ ሱሉልታን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን በናይጄርያዊው አደም እና ብሩክ ጎሎች 2-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ኤርሚያስ ዳንኤል ለሱሉልታ አስቆጥሯል። ወሎ ኮምቦልቻ ከ ለገጣፎ ፣ የካ ከሽረ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ጨዋታዎች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *