​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ደቡብ ፖሊስ መሪነቱን ሲረከብ ዲላ ለመጀመርያ ጊዜ ተሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተደርገው ዲላ ከተማ የመጀመርያ ሽንፈቱን ያስተናገደበት ፣ ደቡብ ፖሊስ መሪነቱን የተረከበበት ሳምንት ሆኖ አልፏል።

ሀላባ ከተማ 2-0 ሀዲያ ሆሳዕና

(አምሀ ተስፋዬ)

በርካታ ደጋፊዎች የታደሙበት እና የሳምንቱ ተጠባቂ የነበረው የሀላባ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በባለሜዳው ሀላባ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታው ፈጣን እንቅስቃሴ እና ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት ቢሆንም በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ እምብዛም የጎል ሙከራዎች አልተስተናገዱበትም። በ8ኛ ደቂቃ ላይ የከፍተኛ ሊግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራ የሚገኘው ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ በመግጨት ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርጎ የሀላባ ግብ ጠባቂ ሶፎንያስ ሲያድንበት በተቀራኒው ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ የዘገዩት ሀላባ ከተማዎች በ25ኛው ደቂቃ ላይ በመሀመድ ናስር አማካኝነት የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ደግሞ መሀመድ ናስር በግምት ከ20 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ማቲዎስ ሰለሞን መልሶበት ወደ ማዕዘን ምት ሲቀይራት ከማዐረዘን የተሻገረውን ኳስ አስቻለው ኡቱ በግንባሩ ቢገጨውም የግቡ ቀኝ ቋሚ መልሶበታል፡፡

ከዕረፍት መልስ ሀላባ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ የበላይነት የነበረው ሲሆን በ56ኛው ደቂቃ ስንታየው መንግስቱ ከርቀት መሬት ለመሬት መትቶ ባስቆጠረው ጎል ዳሚ መሆን ችለዋል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ጉሽሚያ እና አላስፈላጊ የቃላት ልውውጦች በተጫዋቹች ላይ ተስተውሏል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ ላይ ሀላባ ከተማ ተጫዋች ላይ በተሰራው ጥፋት ቅጣት ምት የሰጡት ፌደራል ዳኛ ኢሳያስ ወደወደቀው ተጫዋች ደርሰው በሚያናግሩበት ሰአት የሀዲያ  አሰልጣኝ ኢዘዲን አላስፈላጊ ንግግር በማድረጋቸው ዳኛው የቃል ማስጠንቀቂያ የሰጡት ቢሆንም በድጋሚ ቀጥሎ ጨዋታውን ከማስጀመራቸው በፊት የሀዲያ ቡድን መሪ እንዲሁም 4ኛ ዳኛ እና አሰልጣኝ ኢዘዲንን ከጠሩ በኃላ ምክክር አድርገው አሰልጣኝ ኢዘዲንን ከሜዳ እንዲወጣ አዘዋል፡፡

ውጤቱን ለመለወጥ ተጭነው የተጫወቱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተለይ በ76ኛው ደቂቃ  የሚያስቆጭ የግብ ዕድል አምክነዋል። መሀመድ ያሻገረውን ኳስ ሶፎንያስ ከአየር ላይ ሆኖ ተወርውሮ ቢይዘውም ወደ መሬት በሚወድቅበት ጊዜ ኳሷ ከእጁ በማምለጡ በቅርብ ርቀት የነበረው መለሰ ወደ ግብነት ለወጣት ቢባልም የሀላባ ተከላካይ ናትናኤል ጌታሁን እንደምንም ብሎ አድኖታል፡፡ በ86ኛው ደቂቃ መሀመድ ከድር በመልሶ ማጥቃት ያሻገረውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ ናትናኤል ጌታሁንን አልፎ ቢሄድም ጎትቶ በማስቀረቱ የዕለቱ ዳኛ ቅጣት ምት ብቻ በመስጠታችው የቀይ ካርድ ይገባዋል የሚል ቅሬታቸውን ፌደራል ዳኛ ኢሳያስን ከበው ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጌዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አብነት ተሾመ ኳስን ከመረብ በማገናኘት የሀላባን መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ሲችል ጨዋታውም በሀላባ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጅማ አባ ቡና 0-0 ቡታጅራ ከተማ

(ቴዎድሮስ ታደሰ)

ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ከ ቡታጅራ ከተማ አቻ ተለይተዋል። ባለሜዳዎቹ በተከታታይ በሜዳቸው ነጥብ መጣላቸውንም ቀጥለዋል፡፡ ከአሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሀንስ ጋር የተለያየው ጅማ አባቡና በግብ ጠባቂ አሰልጣኙ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ እቅስቃሴ  በመሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ የጎንዮሽ እና ወደ ኃላ በሚመሱ ኳሶች የበዙበት አሰልቺ እና የሚቆራረጡ ቅብብሎሽ በተደጋጋሚ የተመለከትንበት ነበር። በባለሜዳዎቹ በኩል አልፎ አልፎ የሚገኙትን አጋሚዎች ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች እንዲሁም ቡድኑ ተጫዋቾች ከቡድን ጨዋታ ይልቅ በግላቸው በሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች ጨዋታውን ውበት ያበለሸው ሲሆን ቡድኑ መልበሻ ቤት አሁንም እንዳልተረጋጋ የሚያሳይ ነው። 
በቡታጅራ በኩል በመከለከል ላይ መሰረት ባደረገው አጨዋወታቸው የተቃራኒ ቡድን ከመፈተን ይልቅ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ሰአት ለመግደል የሚደርጉት እቅስቃሴ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። ለዚህም ማሳያ በመጀመሪያው አጋማሽ በ25 ደቂቃ ግብ ጠባቂው የማስጠንቀቂያ ካርድ ሰለባ ሆኗል። በተጨማሪም የቡታጅራዎች የባለሜዳዎቹን አለመረጋጋት በመመልከት የታክቲክ ለውጥ አለማድረጋቸው  የሚስገርም ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ቤት ሊገቡ ችለዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመርያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ በጨዋታ እና በጎል ሙከራ ከመጀመሪያው የተሻለ ሲሆን አባቡናዎች በ49 ፣ በ63 እና 84ኛው ደቂቃዎች ያገኟቸውን የግብ እድሎች ባለመጠቀማቸው እንዲሁም የቡድኑ ተጫዋቾች ተነሳሽነት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወርዶ በመታየቱ የቡድኑ እቅስቃሴላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ቡታጅራዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ሁለት በመልሶ ማጥቃት የተገኙትን አጋጣሚዎች አልተጠቀሙበትም።

በእለቱ በቂ የፀጥታ ኃይሎች በሜዳው ያልተገኙ ሲሆን የእለቱ ኮሚሽነር ብርሃኑ ደምሴ የፀጥታ ኃይል እንዲመጣና ጨዋታው እንዳይቋረጥ ባደረጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይጠባል።

ወደ ወራቤ ያመራው ዲላ ከተማ በውድድር አመቱ የመጀመርያ ሽንፈቱን አስተናግዶ መሪነቱንም ለደቡብ ፖሊስ አስረክቧል። ስልጤ ወራቤ በፈቲ ረሚሼቾ ጎል 1-0 ያሸነፈ ሲሆን ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል መመለስ ችሏል።

ቦንጋ ላይ መቂ ከተማን ያስተናገደው ካፋ ቡና በበረከት ብቸኛ ጎል 1-0 ማሸነፍ ሲችል ወልቂጤ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ፣ ነገሌ ከተማ ከሀምበሪቾ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ደቡብ ፖሊስ አቻ ቢለያይም ዲላ ከተማ በመሸነፉ መሪነቱን መረከብ ችሏል።

ቅዳሜ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ቤንችማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በድሬዳዋ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በዚህ ምድብ ናሽናል ሴሜንት ከሻሸመኔ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *