​ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል

በኢትዮዽያ እግርኳስ ላይ ዘመን ተሻጋሪ አስተዎፅዖ ካበረከቱ የእግርኳስ ሰዎች አንዱ የሆኑት አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተሉ ቆይተው በአሁን ሰአት የጤናቸው ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በመኖርያ ቤታቸው ህክምናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ።

የአሰልጣኝ ስዩም በፍጥነት ከህመማቸው አገግመው ወደሙያቸው እንዲመለሱ እና የተሻለ ህክምና ከሀገር ውጭ እንዲያገኙ ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ የሙያ አጋሮቻቸው የተሰባሰቡበት ኮሚቴ ተዋቅሮ የገቢ ማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ።
በአሁኑ ወቅት ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የገንዘብ ልገሳ እየተደረገ ይገኛል። በሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያ እግርኳስ ተጨዋቾች ማህበር የ100,000 የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚው ሲሆን የተዋቀረው ኮሚቴ ለህዝቡ ይፋ ባደረገው የባንክ አካውንት ልገሳው ቀጥሎ ለረጅም አመት በአሰልጣኝነት ያገለገሉበት የኢትዮዽያ ቡና ስፖርት አመራር ቦርድ በአካል በመሄድ እንደጎበኙና እና የአሰልጣኙ የጤንነት ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ ክለቡ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ሙሉ ወጪን ክለቡ እንደሚሸፍን እና በቀጣይ ለህክምናው የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ስድስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ  ክለቡ ያዋቀረ መሆኑን በመግለፅም በቀጣይ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮዽያ ቡና በሜዳው ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የተመረጠ አንድ ጨዋታን ሙሉ የስታድየም ገቢ እንደሚያደርግ አሳውቋል ። ዛሬ ረፋድ ላይ ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሎ ሙሉ የተጫዋችነት ዘመናቸውን ያሳለፉበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ አመራር የ100,000 ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ በክለቡ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገፅ አስታውቋል።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ባለውለታ የሆኑትን አሰልጣኝ ለመደገፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በጎ ምላሾች እየመጡ መሆኑ ኮሚቴዎቹን እያስደሰተ ሲሆን በቀጣይም ህይወታቸውን ለማትረፍ እና በቂ ህክምና አግኝተው ወደሚወዱት ሙያ ተመልሰው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ድጋፍ እንዳይለየው አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *