ባምላክ ተሰማ ወደ አለም ዋንጫ ስለመጓዝ ተስፋው ይናገራል

ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢንተርናሽናል መድረክ ታላላቅ ውድድሮችን በብቃት እየዳኘ እና እድገቱን እያሳየ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በቅርቡ በሞሮኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ላይ አገልግሎ ተመልሷል። ባምላክ ከቻን መልስ በውድድሩ ላይ ስለነበረው ቆይታ እና በ2018 በሩስያ አስተናጋጅነት ስለሚካሄደው የአለም ዋንጫ የመዳኘት ተስፋው ዙርያ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ ይዘን ቀርበናል ።

በሞሮኮ የቻን ቆይታህን እንዴት አገኘህው ከሩዋንዳው ውድድር ምን የተለየ ነገር አገኘህበት ?

ቻን ጥሩ ነበር። በዋና ደኛ በመሆን ሁለት ጨዋታ ነበር ያጫወትኩት። አንጎላ ከቡርኪናፋሶ የምድብ ማጣርያ በመቀጠል የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ሱዳን ከ ዛምቢያ ጋር ነው። ከዛ ውጪ የፍፃሜ ጨዋታ ሞሮኮ ከ ናይጄሪያ እና ሌሎችን ጨዋታዎች ጨምሮ በአራተኛ ዳኝነት መምራት ችያለው። ከባለፈው አመት አኳያ ለውጡ በፍፃሜ ጨዋታ ዘንድሮ በአራተኛ ዳኝነት መምራቴ እንጂ ከባለፈው ውድድር ተመሳሳይ ነው። የተለየ ነገር የለውም ፤ ከሩብ ፍፃሜ ተሻግሬ ሌላ ጨዋታ ባጫውት መልካም ነበር። ያም ባይሆን ጥሩ ጊዜ ነበር ።

ከሞሮኮ የቻን ውድድር ቆይታህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አልተመለስክም። ይልቁንም ለከፍተኛ ስልጠና ወደ ሌላ ሀገር አምርተሀል። የት ሀገር ነው ስልጠናው ? ቆይታህስ እንዴት ነበር ?

በዛው ነው ለስልጠና ወደ ኳታር የሄድኩት። የአንድ ሳምንት ቆይታዬ በጣም ትልቅ ስልጠና ነበር ። ስልጠናው ያተኮረው በአካል ብቃት የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶች እና በተለይ የቪዲዮ ( የምስል ) ማሳያ ዳኝነትን ላይ ሲሆን ስልጠናውም የቀጣይ አለም ዋንጫን አስመልክቶ የተሰጠ ነው ። ፈተናዎችም ነበሩት። ብዙ አዳዲስ ህጎችን ፣ ዕውቀቶች አግኝቼበት ነው የተመለስኩት ።

በአለም ዋንጫ ከአፍሪካ አሁጉር የመጨረሻ እጩ ሆነው ከቀረቡት ስድስት ዳኞች መካከል አንዱ ነህ ። መቼ ነው የአለም ዋንጫ ዳኞች የሚታወቁት ?

ገና ነው የመጨረሻ ዳኞች የሚታወቁበት። እንደነገሩን ከሆነ በፈረንጆች አቆጣጠር March 25 በእኛ ወደ መጋቢት 16 ላይ ይገለፃል ተብሏል። በአለም ዋንጫውም የቪዲዮ ዳኝነት ይደረግ አይደረግ ገና አልተወሰነም። ፊፋ በአለም ዋንጫው ላይ የመጀመር ሀሳብ አለው። ከዛ ጋር በተያያዘ ነው ቀኑን መግፋት የፈለጉት ።

በኳታር የተሰጠው ፈተና ለአለም ዋንጫው ምርጫ አስተዋፆኦ አለው ?

በጣም አለው። ስልጠናው ሙሉ ትኩረቱ የአለም ዋንጫን መሰረት ያደረገ ነው። ፈተናውንም በተገቢ ሁኔታ ጨርሼ መጥቻለው። ከፈጣሪ ጋር መልካም ነገር እጠብቃለው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *