​ሪፖርት | በሁከት በተጠናቀቀው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ አቻ ተለያይተዋል 

በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተተካይ መርሃግብር ዛሬ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስንና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በተፈጠረ ከፍተኛ የደጋፊዎች ሁከት ታጅቦ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሚታወቁበት የ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ሲጀምሩ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ካደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ ምንተስኖት አዳነን በአዳነ ግርማ የተቀየረ ሲሆን በዛው ጨዋታ ላይ ጉዳት ገጥሞት ተቀየሮ የወጣው አስቻለው ታመነ በሳላዲን ባርጌቾ እንዲሁም በሀይሉ አሰፋ ከረዥም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ በተመለሰው አሜ መሀመድ ተተክተዋል። አዳማ ከተማዎች በ4-2-3-1 ቅርፅ ጨዋታውን ሲጀምሩ ባሳለፍነው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ የሶስት ተጨዋቾች ቅያሪን አድርገዋል። በዚህም መሠረት ቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ  አንዳርጋቸው ይላቅን በሱሌይማን ሰሚድ ፣ ተስፋዬ በቀለን ከጉዳት በተመለሰው ሙጂብ ቃሲም እንዲሁም የመስመር አማካዩ ሲሳይ ቶሊን በኤፍሬም ዘካርያስ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቷል።

ሁለቱም ቡድኖች በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል ፤ በተለይም አዳማ ከተማ ከመጀመርያ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ በአማካይ እንዲሁም በአጥቂ ስፍራ ላይ ፈጣን በሆኑ ወጣት ተጫዋቾች እንደመዋቀሩ በጨዋታው በእጅጉ ተጋላጭ ለነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች አስደናቂ ፍጥነታቸውን በመጠቀም ፈተና ሲሆኑባቸው ተስተውሏል፡፡

አዳማ ከተማዎች የመጀመሪያውን አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ለማድረግ የወሰደባቸው 9 ያክል ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ። ጋዲሳ መብራቴ ለሙሉአለም መስፍን አቀብላለው ብሎ የተሳሳተውን ኳስ በጨዋታው እጅግ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያመሸው ቁመተ መለሎው ከነአን ማርክነህ ነጥቆ ሁለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰችበት ኳስ የመጀመሪያዋ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡
በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው አንጻር ደካማ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ከጨዋታ እንቅስቃሴ የፈጠሯት ብቸኛ የግብ ማግባትን አጋጣሚ በ11ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከአዳማው ግብጠባቂ ጃኮብ ፔንዜ ጋር ተገናኝቶ ኳሷን ከግብጠባቂው አናት በላይ ለማሳለፍ ሞክሮ ጃኮብ ያዳናት ኳስ ብቻ ነበረች፡፡

በጨዋታው 18ኛ ደቂቃ ላይ የአዳማው ሁለገቡ ተጫዋች ሙጂብ ቃሲም ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ዳግም ባጋጠመው ጉዳት በአንዳርጋቸው ይላቅ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡ ይህም ቅያሬ በመጀመሪያው የቡድኑ ቅርፅ ውስጥ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረው ሱሊይማን ሀሚድ በመጂብ ምትክ ወደ መሀል ተከላካይነት እንዲጫወት ሲገደድ በአንጻሩ ሙጂብን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባውና የቀድሞውን አሳዳጊ ክለቡን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃራኒ የገጠመው አንዳርጋቸው ይላቅ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የቀሩትን ደቂቃዎች ለመጫወት ችሏል፡፡

ብልጫ ወስደው መጫወታቸው የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁቴሳ በመስመሮች መካከል ያገኘውን ሰፊ ክፍተት ተጠቅሞ የተቀበለውን ኳስ ወደፊት ገፍቶ ከጊዮርጊስ የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ተረባርበው ወደ ውጪ አወጡበት እንጂ ጠንካራ የግብ ሙከራ ነበረች፡፡ ከዚች ሙከራ ሁለት ደቂቃዎች በኃላ ማለትም በ26ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል ዳዋ ሆቲሳና ከነአን ማርክነህ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ከደረሱ በኃላ ባሳለፍነው ክረምት አዲስአበባ ከተማን ለቆ አዳማን የተቀላቀለው ከነአን ማርክነህ ሰልሀዲን በርጌቾን አታሎ በግሩም አጨራረስ ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ይበልጥ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ37ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ሊያሳድጎበት የሚችሉበትን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ቢያገኙም በረከት ደስታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

መሀል ለመሀል እንዲሁም በመስመሮች በኩል በሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በኩል ፍፁም ተዳክመው የተስተዋሉት ፈረሰኞቹ በግራ መስመር አጥቂያቸው ጋዲሳ መብራቴ በመከላከል እንዲሁም ቡድኑ ወደፊት በመሄድ የግብ እድሎችን እንዲፈጥር በግሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ከግራ መስመር ያሻማውን የማእዘን ምት አብበከር ሳኒ በነጻ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢገጭም ወደ ግብ የላካት ኳስ ግን ኢላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች፡፡
በመጀመሪያ አጋማሽ በአስገራሚ ሁኔታ በ3 አጋጣሚዎች ላይ የመጫወቻ ኳሶቹ ከተፈቀደው የአየር መጠን በታች አየር በመያዛቻው በቅዱስ ጊዮርጊሱ አምበል ደጉ ደበበ ጥያቄ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተቋርጦ እንዲቀየሩ ተደርገዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፖርቹጋላዊው ቫዝ ፔንቶ በመጀመሪያው አጋማሽ በፊት አጥቂነት ሲጫወት የነበረው አሜ መሀመድን አስወጥተው የመስመር አጥቂው በኃይሉ አሰፋን ማስገባት ችለዋል ፤ በዚህም ለውጥ ምክንያት በመጀመሪያው አጋማሽ በቀኝ መሰመር አጥቂነት ሲጫወት የነበረው አቡበከር ሳኒ ወደ ፊት አጥቂነት ሊሸጋሸግ ችሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በተለይ አዳማ ከተማዎች በበርካታ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በቁጥር ብልጫን በመውሰድ በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ላይ መገኘት ቢችሉም በተጫዋቾቻቸው እጅግ ደካማ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር እድሎቹን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ያለ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ አማካዩ አዳነ ግርማን አስወጥተው አጥቂውን ኢብራሂም ፎፉናን በማስገባት በ4-2-4 ቅርፅ የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን በማብዛት ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ አልነበረም፡፡ ፊት ላይ ያነበሩት አራቱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ያላቸው ደካማ የሆነ የአየር ኳስን የማሸነፍ ንጻሬ ጋር ተዳምሮ በቀጥተኛ አጨዋወት እንዲሁም ሁለቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ለነዚሁ አጥቂዎች በቂ የሆነ የኳስ ማቅረብ አለመቻላቸውን ተከትሎ አራቱ ተጫዋቾች ሲባክኑ ተስተውሏል፤ በተጨማሪም አራቱ አጥቂዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ኳስ በሚያጣበት ወቅት በመከላከሉ ላይ ለመሳተፍ ያላቸው ተነሳሽነት ደካማ መሆኑን ተከትሎ አዳማ ከተማዎች በመሀል ሜዳ ላይ ያላቸውን ብልጫ ለመጠቀም ጥረት አላደረጉም እንጂ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጋላጭነት ከፍ ያደረገ ቅያሬ ነበር፡፡

የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አራት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩ በአዳማ የግብ ክልል ግራ ጠርዝ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን ቅጣት ምት በኃይሉ አሰፋ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ በአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ደካማ የቋመ ኳስን የመከላከል ስርአት መሠረት በጣም በቅርብ ርቀት ውስጥ በነጻ አቋቋም ላይ ይገኙ ከነበሩት አራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች መካከል አብበከር ሳኒ አግኝቶ በማስቆጠር ቡድኑን በሜዳው ከመሸነፍ የታደገች የአቻነት ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ በ87ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ያገኙትን የማእዘን ምት ለመምታት የአዳማው የመስመር አጥቂ የሆነው በረከት ደስታ ወደ ማእዘን ምት መምቻው በሚያቀናበት ወቅት ከተወሰኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በተወረወረበት ቁሳቁስ የማእዘን ምቱን መምታት ባለመቻሉ ጨዋታውን የመሩት ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ ጨዋታውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ በዚህ ቅፅበት በተለምዶው ሚስማር ተራና የካታንጋ አዋሳኝ አጥር አቅራቢያ ይገኙ የነበሩት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል በተቀሰቀሰ ሁከት በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ለጉዳት ተዳርገዋል። በዚህም ግጭት የተነሳ ጨዋታው ለ28 ያክል ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል ፤ በተቋረጠበት አጋጣሚ በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ካልሆኑ ደጋፊዎች ወደ ተጫዋቾች በተወረወረ ቁስ የቡድኑ የተከላካይ አማካይ ሙሉአለም መስፍን ተመቶ ሜዳ ውስጥ ተዘርሮ ለመመልከት ችለናል፡፡

ግብ አስቆጣሪዎቹ ከነአን እና አቡበከር

ከከ28 ደቂቃዎች መቋረጥ በኃላ አልቢትሩ የቀሩትን ሶስት ደቂቃዎች አጫውተው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም በስታዲየሙ የታደሙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በተጫዋቾቻቸው እንዲሁም አሰልጣኝ ቡድን አባላት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞቸውን አሰምተዋል፡፡

በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የተነሳ የአሰልጣኞቹን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *