ወላይታ ድቻ ሁለት የውጪ ተጨዋቾቹን አሰናበተ

ወላይታ ድቻ በክረምቱ ካስፈረማቸው የውጪ ተጨዋቾች መካከል ቻዳዊው ተከላካይ ማሳማ አሴልሞ እና ናይጄሪያዊው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮን እንዳሰናበተ የክለቡ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ወላይታ ድቻ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቻዳዊው የመሀል ተከላካይ ማሳማ አሴልሞን እና ናይጄሪያዊውን የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮን ቢያስፈርምም በክለቡ ያሳዩት አቋም ከተጠበቀው በታች የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ከለክቡ ጋር ተለያይተዋል። አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ስለተጨዋቾቹ ስንብት ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት የመሀል ተከላካዩ ማሳማ አሴልሞ እስከ አሁን ተጎዳው በማለት በርካታ ጨዋታዎች ያመለጡት ሲሆን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ከሀገራችን ተጫዋቾች የተሻለ አለመሆኑ እና አስቀድሞ ጉዳት የገጠመው እንደሆነ ገልፀዋል። ተጨዋቹ እስካሁን ወላይታ ድቻን በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ማገልገሉም (በጨዋታው ተቀይሮ ገብቶ በድጋሚ ተቀይሮ ወጥቷል።) ለስንብቱ ተጨማሪው ምክንያት ሆኗል። 

ሌላኛው ተሰናባች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ረጅም አመት የቆየው ናይጄሪያዊው ግብ ጠባቂ ማኑኤል ፌቮ በአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ተመራጭ ያልሆነ ተጨዋች ነው። ፌቮ በውድድር ዘመኑ ጥቂት ጨዋታዎች ብቻ ያደረገ ሲሆን  አሰልጣኙ እደገለፁት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያልተሰጠው ሲሆን በቀጣይ ቀናት ክለቡን እንደሚሰናበት አስረድተዋል። አሰልጣኙ ለስንብቱ እንደምክንያት የገለፁት በሜዳ ላይ የሚያሳየው ፌዘኛ የልምምድ እንቅስቃሴ ፣ እድሜው መግፋቱ እና የመስራት ፍላጎቱ እጅግ የወረደ መሆን ሲሆን ይህም ሌሎች ተጫዋቾች ላይ ተፅእኖ የሚያመጣ በመሆኑ ተመራጭ ግብ ጠባቂ እንዳላደረጉት ተናግረዋል። አሰልጣኙ ግብ ጠባቂው ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንዳይሰራ ለክለቡ ጥያቄ አቅርበው ከክለቡ እንዲለያይ ማድረጋቸውንም ጨምረው ተናግረዋል። 

ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን የፊታችን ረቡዕ ዚማሞቶን በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም የሚያስተናግድ ሲሆን ለዚህም ሀዋሳ ገብቶ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ልምምዱን ማድረግ ጀምሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *