ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ከመሪው ያለውን ልዩነት ያጠበበበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የ7ኛ ሳምንት ተስተተካይ መርሃ ግብር ዛሬ በ8 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው መከላከያ 2ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

ጨዋታው እንደተጀመረ ገና በ5ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያዋ አማካይ ኤልሻዳይ ግርማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ በግሩም ሁኔታ አክርራ በመምታት ማራኪ የሆነችን ግብ በማስቆጠር ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበረው አመዛኙ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታው ወደ መከላከያ የሜዳ አጋማሽ አድልቶ መካሄድ ችሏል። ነገርግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ላይ እንዳደረጉት በርካታ የኳስ ቅብብሎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ላይ በመድረስ ግን አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንጻሩ መከላከያዎች ያላቸውን ልምድ በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡

ከፍተኛ የግብ ሙከራዎች እጥረት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ36ኛው ደቂቃ ላይ ትመር ጠንክር ከማዕዘን የተሻማላትን ነፃ ኳስ ያመከነችው አጋጣሚ ብቻ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አጥቂዋ መዲና አወልን ቀይረው ያስገቡት መከላከያዎች በመጀመሪያ አጋማሽ እጅግ ተነጣጥሎ የነበረውን የቡድኑ የአጥቂና የአማካይ ክፍልን ለማገናኘት ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ተስተውላለች። በመጀመሪያ አጋማሽ የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ በሁለተኛው አጋማሽ ማስመለስ የቻሉት መከላከያዎች በ66ኛው ደቂቃ ምስራች ላቀው ከረጅም ርቀት እጅግ ግሩም የሆነች ግብን አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችላለች፡፡

ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መከላከያዎች በሄለን እሸቱና በመዲና አወል ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን ወደ 17 በማሳደግ ከመሪው ደደቢት የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ 4 ዝቅ በማድረግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *