​ሪፖርት | ቡና እና ሀዋሳ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች ነጥብ ተጋርተዋል 

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድራማዊ ክስተቶች ባስተናገደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ መቐለ አቅንቶ ከመቐለ ከተማ ጋር 0-0 ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሶስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው በ4-2-3-1 አሰላለፍ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። አማካይ ስፍራ ላይ ክርዚስቶም ንታምቢ መስኡድ መሀመድን በመተካት ሲሰለፍ በተመሳሳይ ሳምሶን ጥላሁንና አማኑኤል ዮሀንስም በአቡበከር ናስር በእያሱ ታምሩ ተተክተዋል፡፡ በአንጻሩ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ከ13 ቀናት በፊት ወደ አዲግራት አቅንቶ በወልዋሎ ከተሸነፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ በተከላካይ መስመር ላይ ዮሀንስ ሰጌቦ ደስታ ዮሀንስን በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ በአጥቂ ስፍራ ላይ በዳዊት ፍቃዱ ምትክ ፍርዳወቅ ሲሳይ በማስገባት በ4-2-3-1 ቅርፅ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በግብ ሙከራዎች የታጀበ ባይሆኑም በመሀል ሜዳ ላይ ባመዘነ መልኩ በርካታ የኳስ ንክኪዎችን በማድረግ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በጨዋታው እጅግ ጥቂት የሚባሉ የጠሩ የግብ እድሎችን ቢፈጥሩም ባለሜዳዎቹ ኢትዮጽያ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በተለይም ሳሙኤል ሳኑሚ በመጀመሪያው 10 ደቂቃ ውስጥ በተሻለ ቦታ አያያዝ ላይ በመገኘቱ ያገኛቸውን ሁለት ጥሩ ጥሩ ኳሶች በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ ያመከናቸው እንዲሁም ኤልያስ ማሞ ከሀዋሳ የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ለግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ 22ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ተጫዋቾችን ስህተት ተጠቅሞ አቡበከር ነስሩ ሳይጠቀምባት የቀረችው ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ የምታስቆጭ ነበረች።

ፈጣኑ እስራኤል እሸቱን በብቸኛ አጥቂነት በተጠቀሙት ሀዋሳ ከተማዎች በኩል ተጫዋቹ በተናጥል የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ሲፈትን ተስተውሏል። ከኳስ ውጪ ካለው ፋታ የለሽ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በቡድን አጋሮቹ በቂ ድጋፍ ባያገኝም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳሱን ከራሳቸው ግብ ክልል ጀምረው እንዳይወጡ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ይህ ነው የሚባል የጎል ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ባልቻሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንጋፋው አማካይ ሙሉዓለም ረጋሳ የቡድኑን የኳስ ስርጭት በመቆጣጠር በኩል ከፍተኛ ሚናን ተወጥቷል፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጨዋታው እጅግ እየተቀዛቀዘ ሄዷል። ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች በ40ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ ያሻማውን ኳስ የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች የሆነው አክሊሉ ዋለልኝ ጨርፎ ወደ ግብ ቢሞክራትም ኳሷን በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ በቀላሉ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ የያዘበት በመጀመርያው አጋማሽ ከሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች መካከል ነው፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባልን እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል፡፡ ሆኖም ሀዋሳዎች ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ከሜዳቸው ውጪ እንደመጫወታቸው ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት በመጠኑም ቢሆን ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ እያሱ ታምሩን አስወጥተው መስኡድ መሀመድን ካስገቡ በኋላ በተሻለ ወደ ጎል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡

የመስኡድ ቅያሪ ቡድኑን ወደ ኃላ ያፈገፈገውን የሀዋሳ የመከላከል አደረጃጀት በሜዳው የላይኛው ክፍል ይፈልገው የነበረውን የተለጠጠ ስፋት ያሳጣ ቢሆንም ተጫዋቹ ተቀይሮ ከገባበት ደቂቃ አንስቶ ከፍተኛ ርቀት በማካለል ጥረት ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይም የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና የጨዋታውን ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ በእጃቸው በማስገባት የሀዋሳ ከተማን ግብ በተደጋጋሚ መፈተሽ ችለዋል። በ80ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ወደ ግብ ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ አክሊሉ አክርሮ የመታውን ሜንሳህ ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ሲሆኑ በተመሳሳይ በ82ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በ86ኛው ደቂቃ ላይ ክሪዚስቶም ንታምቢ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መስኡድ መሀመድ ከሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካት ኳስ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችላ ስታድየሙን በከፍተኛ ደስታ እንዲዋጥ አድርጎታል፡፡

የመስዑድ ጎል ቡናን ድል ለማስጨበጥ እንዲቃረብ ቢያደርገውም ደስታው የዘለቀው ለሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ88ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ወደ ቡና የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በጨዋታው በሀዋሳዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እስራኤል አሸቱ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ሀሪሰን ሄሱ በአስገራሚ ብቃት ቢያድንበትም በቅርብ ርቀት የነበረው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ሀዋሳን አቻ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሯል።

ከጎሎቹ በኋላ ተጨማሪ ደቂቃውን ጨምሮ በነበሩት ቀሪ ስድስት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች የማሸነፊያዋን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካለቸው ቀርቷል፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን ማሻሻል የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበተ ቀርቷል። በዚሀም መሠረት ኢትዮጵያ ቡና በ20 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በአንጻሩ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ሀዋሳ ከተማ በ15 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *