​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | በአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

በ7ኛ ሳምንት ሊደረግ መርሀ ግብር ወጥቶለት በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ምክንያት ሳይደረግ የቀረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ዛሬ አአ ስታድየም ላይ ተካሂዶ በእንግዳው ቡድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የአንደኛው ዙር ጨዋታዎችም በዛሬው እለት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀዋል።

09:00 ላይ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተቆጠሩት ጎሎች ውጪ የጎል ሙከራዎች ያልታዩበት ፣ እጅግ የተቀዛቀዘ እና በመሀል ሜዳ የተገደበ እንቅስቃሴ ታይቶበታል። በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበራቸው ሀዋሳዎች በግራ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ የጎል እድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በ43ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰችው መሳይ ተመስገን ከግራ መስመር ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል የላከችው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ግብነት በመቀየር ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው የተለየ እንቅስቃሴ ያልተስተዋለበት ሲሆን ሀዋሳዎች ወደ ግብ በመቅረብ የተሸመሉ ነበሩ። በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካ ሆኖ ታይቷል። በ80ኛው ደቂቃ አምበሏ ምርቃት ፈለቀ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አጥብባ ለመግባት ስትሞክር በተሰራባት ጥፋት ከተገኘው ቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ቅድስት ዘለቀ ወደ ግብነት ቀይራ የሀዋሳን መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ችላለች። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ውጤቱ ሀዋሳ ከተማን ከወራጅ ቀጠናው ሲያወጣው እየተሳተፈባቸው በሚገኝባቸው የተለያዩ ሊጎች ላይ መጥፎ የውድድር አመት እያሳለፈ የሚገኘው ኤሌክትሪክን በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ አስቀምጦታል።

የመጀመርያው ዙር በዚህ መልኩ ተጠናቋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *