​ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነፍስ ዘርቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረው እና በተስተካካይነት የተያዘው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬደዋ ከተማ ጨዋታ ዛሬ ምሽቱን ተደርጎ በባለሜዳዎቹ የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሲዳማ ተጉዞ አቻ ከተለያየበት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲሴ ሀስንን እና በሀይሉ ተሻገርን በምንያህል ይመር እና ተክሉ ተስፋዬ የተካ ሲሆን ድሬደዋ ከተማ ደግሞ ወልዋሎ ዓ.ዩን ካሸነፈበት ጨዋታ በወሰኑ መዜ ምትክ ለሳውሬል ኦልሪሽ ጨዋታውን የመጀመር ዕድል ሰጥቷል። 

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየባቸው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም ኳስ መስርተው ወደ ፊት ለመሄድ ይሞክሩ የነበሩበት ሁኔታ በማሸነፍ ላይ የተመሰረተ የጨዋታ ዕቅድ ይዘው ለመግባታቸው ማሳያ ነበር። የተወሰኑ ደቂቃዎች ካለፉ በኃላ ግን ወደ ተቃራኒ ሜዳ ተጭኖ በመግባቱ በኩል ይበልጥ ጉልበት እያገኘ የመጣው የባለሜዳዎቹ ጥቃት ነበር። በተለይ ጫላ ድሪባ ባልተለመደ መልኩ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈበት የቡድኑ የቀኝ ኮሪደር ይበልጥ የጥቃቱ ምንጭ ሆኖ ታይቷል። በዚህ በቀኝ መስመር ባደለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የተክሉ ታፈሰ ሚናም ከፍተኛ ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራም ጫላ ድሪባ ከዚሁ አቅጣጫ ወደ ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ በጎን ሲወጣበት የተገኘ ነበር። የኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጫና በርትቶ በቀጠለባቸው በነዚህ ጊዜያትም 20ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ በቀጥታ የቅጣት ምት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ተክሉ ታፈሰ ከምንያህል ይመር ቅጣት ምት በግንባሩ ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው። 

በሂደት የተወሰደባቸውን ብልጫ መቀንስ የቻሉት ድሬደዋ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥራቸው እስከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሳጥን ድረስ ዘልቆ መግባት ባይችልም 27ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ኢሳያስ ከርቀት አክርሮ የመታት ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ ግን ሳትነሳ አታልፍም። ቡድኑ በማጥቃት ላይ ብዙ ሲሳታፍ የነበረውን እና በአወት ገ/ሚካኤል እና ጥላሁን ወልዴ ጉዳት ሳቢያ በጫላ ድሪባ የተሸፈነውን የተጋጣሚው ደካማ የመከላከል ቀኝ መስመር ላይ ያተኮረ የማጥቃት ሂደትን አለመከተሉ ግልፅ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር አድርጎታል። ከተከላካዮች ፊት የነበረው የኢማኑኤል ላርያ እና ሳውሬል ኦልሪሽ ጥምረትም ካሉሻ አልሀሰንን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ድሬዎችን ከቀጥተኛ ጥቃት ቢታደግም በማጥቃት ሂደት ላይ ለዘላለም ኢሳያስ ፣ ዬሴፍ ደሙዬ እና ሙየዲን ሙሳ ጥምረት የነበረው እገዛ እጅጉን ደካማ ነበር። በዚህም የተነሳ አጥቂው አትራም ኩዋሜ ከአማካይ ክፍሉ ተነጥሎ እንቅስቃሴው በቀላሉ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ጥላ ስር እንዲወድቅ ሆኗል። በመከላከሉ ረገድ ግን ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ድሬዎች ከ22ኛ ደቂቃው የተክሉ ሙከራ በኃላ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተነሳን ኳስ አዲስ ነጋሽ ጨርፎት ለጥቂት ከወጣበት አጋጣሚ ውጪ ተጨማሪ አስደንጋጭ ሙከራ ሳይደረግባቸው ነበር ቡድኖቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው እጅግ የተሻለ ፉክክር የተደረገበት እና የጨዋታውም ፍጥነት ጨምሮ የታየበት ነበር። ጨዋታው ከእረፍት በቀጠለበት 46ኛው ደቂቃ ላይም የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አጥቂ ኃይሌ እሸቱ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ በግራ መስመር ይዞ በመግባት በጥሩ እጨራረስ ለቡድኑ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ ፍጥነታቸውን ጨምረው ወደ ኤሌክትሪክ የመከላከል ዞን ለመግባት ጥረት የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ ሁለት ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በዚህም 50ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ዘውድነህ በረዥሙ የጣለውን ኳስ ሙየዲን ሙሳ ከቅርብ ርቀት የሞከረ ሲሆን ሳውሬል ኦልሪሽም በዚሁ ደቂቃ ከረዥም ርቀት ሌላ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ያሳዩትን መነቃቃት ለማስቀጠል በማሰብ ሳውሬል ኦልሪሽን በመሀመድ ጀማል ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮች ቁጥር ያበራከቱት ድሬዎች እንዳሰቡት ስኬታማ መሆን ግን አልቻሉም። 

አብዛኛው የኳስ ቅብብላቸው በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ባመሸው የኤሌክትሪኩ አምበል አዲስ ነጋሽ ሽፋን ሲሰጠው የነበረውን የተጋጣሚያቸውን የኃላ መስመር ለማለፍ የሚያስችል አልነበረም። ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ቢሆኑ ከሚቀሟቸው ኳሶች ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ፈጥረው እና በቁጥር ተመጣጥነው በድሬደዋ አጋማሽ ላይ የሚታዩባቸው ጊዜያት በርካታ ቢሆኑም ከኃይሌ እሸቱ ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ተቀይሮ ከገባው ስንታየው ሰለሞን ይነሱ የነበሩ ኳሶች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚውን ወደ መጨረሻ የግብ ዕድል ለመቀየር የሚያበቁ አልነበሩም። ያም ቢሆን እስከ 69ኛው ደቂቃ ድረስ የነበረው የቡድኖቹ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ተመልካቹን ያዝናና ነበር። 

69ኛው ደቂቃ ላይ የስታድየሙ ፓውዛዎች መጥፋት እና ለቀጣይ 24 ደቂቃዎች መቋረጥ የጨዋታውን ድምቀት እንዳያጠፋው ስጋት የነበረ ቢሆንም መብራቱ ተመልሶ ሲመጣም ጨዋታው ተመሳሳይ የፉክክር መንፈስን ይዞ መቀጠል ችሏል። ሆኖም ከመብራቱ መጥፋት በፊት የነበረው የቡድኖቹ ደካማ ጎን የቀጠለ ሲሆን በባለሜዳዎቹ በኩል 75ኛው ደቂቃ ላይ ኃይሌ እሸቱ በግራ መስመር በፍጥነት በመግባት  ጀማል ጣሰውን አልፎ በሳተው ኳስ ለጎል እጅጉን ቀርበው ታይተዋል። ከዚህ ውጪ ግን ቡድኑ ክፍተት በሚያገኝባቸው አጋጣሚዎች ከወትሮው የወረደ አቋም ላሳየው ዲዲዬ ለብሪ ይላኩ የነበሩት ኳሶች ሲባክኑ ነበር ያመሹት። ሰዐት በገፋ ቁጥር ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀም የጀመሩት ድሬዎችም ጫና መፍጠራቸውን ቢቀጥሉም አሁንም ከሱለይማና አቡ ፊት ግልፅ ዕድል ማግኘት ሳይችሉ እና የገኟቸውን የቆሙ ኳሶችም በአግባቡ ሳይጠቀሙ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

በውጤቱም ነጥቡን 13 አድርሶ ከዛሬ ተጋጣሚው ዕኩል የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመጨረሻ ደረጃ ወደ 14ኛነት ከፍ ያለ ሲሆን ድሬደዋ ከተማ በበኩሉ በነበረበት የ13ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ኤርሚያስ ተፈሪ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ጨዋታው ከታች ወደ ላይ ለመውጣት ለሁለታችንም በጣም ወሳኝ ነበር። ውጥረትም ነበረው። ነገር ግን የተሻልን ስለነበርን አሸንፈን ልንወጣ ችለናል። ያገኘነው ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ፋይዳው ብዙ ነው። በተጨዋቾቻችን ላይ የአሸናፊነት ስነልቦናን ለማስረፅም ጠቀሜታ አለው። ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጅታችንም ዛሬ ማሸነፋችን ወሳኝ ይሆናል። 

አሰልጣኝ ስምኦን አባይ – ድሬደዋ ከተማ

በጨዋታው እንሰራዋለን ብለን ያሰብነውን ነገር መስራት አልቻልንም። ቡድናችን ከብዙ ነገሮች ጋር እየታገለ ነው የሚጫወተው። ከነበረው የፕሮግራም አካሄድ ጋር እና ከተጨዋቾች ጉዳት ጋር ያለውን ነገር ይዞ እየተጓዘ ነው ያለው። ቢሆንም ግን ዛሬ ይዘነው የገባነውን ነገር መተግበር አልቻልንም። በእንቅስቃሴውም ደስተኛ አይደለሁም። እነሱም ያን ያህል ጎልተው መውጣት ባይችሉም ዕቅዳችንን አለማሳካታችን እንድንሸነፍ አድርጎናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *