​” ከጎኔ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ብቃት ችሎታዬ እንዲጎላ እገዛ አድርጎልኛል ”  ከነዓን ማርክነህ

በ2010 የውድድር አመት ድንቅ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ይህ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በስሙ 4 ጎሎች ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበልም  ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ባለፈው ሐሙስ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረገው ጨዋታ እርሱ ባስቆጠራት ጎል ቡድኑ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።  ይሁን እንጂ በጨዋታው ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ያሳየው እንቅስቃሴ ልዩ ነበር። ከስፖርት ቤተሰቡም አድናቆት ተችሮት ነበር። ይህ ተጫዋች የአዳማው 8 ቁጥር ለባሽ ከነአን ማርክነህ ነው። ተጨዋቹ ስለ ወቅታዊ አቋሙ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አምና በአዲስ አበባ ከተማ ከነበረህ ቆይታ ይልቅ ዘንድሮ ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየህ ትገኛለህ። ይህ መሻሻል ከምን የመጣ ነው?  

አምና በአዲስ አበባ ከተማ በነበረኝ ቆይታ በመጀመርያው ዙር ላይ ባጋጠመኝ ጉዳት ረዥም ጊዜ ከሜዳ ዕርቄ ነበር ፤ ወደ አራት ወር የሚጠጋ ጊዜ ማለት ነው። ያም አቋሜ ጥሩ ሆኖ እንዳይቀጥል ተፅዕኖ አድርጎብኛል። አሁን ያለሁበት ክለብ አዳማ ካለው ስብስብ እና ከጎኔ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ጥሩ አቅም ያላቸው መሆናቸው እኔን አጉልቶ እንዲያወጣኝ እገዛ አድርጎልኛል።

ከ20 አመት በታች የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታህን ኢትዮዽያ ከሶማሊያ ጋር ስትጫወት ተቀይረህ ገብተህ ባሳየኸው ጥሩ ያልሆነ እንቅስቃሴ ከስፖርት ቤተሰቡ ተቃውሞ ቀርቦብህ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሴካፋ ዋንጫ ኬንያ ሄደሀል (የመጫወት ዕድል ባታገኝም) እስቲ ያንን ጊዜ እና አሁን ያለውን ነገር አስታውሰህ ንገረኝ? 

በመጀመርያ በብሔራዊ ቡድን መመረጥ በራሱ ያለው ስሜት ትልቅ ነገር ነው። የአንተንም በእግርኳስ ያለህን ስም ከፍ የሚያደርግ ነው ። ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የነበረኝ ተሳትፎ ያው ልጅነት ስለነበረ በትልልቅ ውድድሮች የመጫወት ልምድ ስላልነበረኝ ከብዶኝ ነበር ። ከዛ በመቀጠል ለሴካፋ ጨዋታ ነው ጥሪ የተደረገልኝ። በሴካፋም በጣም ልዩነት አለው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የሚገኙበት ነው። በብዙ ነገር ከታዳጊ ቡድኑ ጋር  ልዩነት አለው ። በሴካፋም የመሰለፍ እድል ቢሰጠኝ ጥሩ ነገር እሰራለው ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም የመሰለፍ እድል ባላገኝም በቡድኑ ውስጥ መካተቴ ለእኔ በስነ ልቦና ረገድ ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጎልኛል።

በጥሩ አቋም ላይ ትገኛለህ። ከምንም በላይ ተረጋግቶ በመጫወት የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ እየሆንክ መጥተሀል። በዚህም ከተመልካቹ አድናቆት እየቀረበልህ ይገኛል። ይህ አቋምህ በልምምድ ወይስ  የመሰለፍ ዕድል በተደጋጋሚ ማግኘትህ የመጣ ነው ?

በአዳማ ተስፋ ቡድን እያለሁ በአሰልጣኝ ኤፍሬም እየተመራን በነበረበት ወቅት ይሰጠኝ የነበረው ሚና እንደፈለኩ በነፃነት እንድጫወት ያደርገኝ ነበር። ይህን ክህሎት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  ያዳበርኩት ይመስለኛል። ለእግርኳስ ተጨዋች ዋናው መሰረትህ ነው ፤ መሰረትህን ይዘህ የምታድግ ከሆነ ያኔ የምታሳየውን አሁን ላይ ማሳየት አይቸግርህም። ይህ ነገር አሁን ላለው ነገር ረድቶኛል ብዬ አስባለው። በተጨማሪም ደግሞ ቡድኑ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች እኔ ጥሩ ነገር እንድሰራ ከፍተኛ አስተዋፆኦ አድርገውልኛል ።

የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ነህ። እንደተሰጠህ ሚና ለጎል የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ የማቀበል ኃላፊነትህን እየተወጣህ ትገኛለህ። ከዚህ ባሻገር እስካሁን በስምህ አራት ጎል አስቆጥረሀል። ይህ ጎል የማስቆጠር አቋምህን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

ጎል የማስቆጠር ጉዞዬ በተወሰነ መልኩ የቀነሰው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው። ያኔም ቅድም እንዳልኩሁ ጉዳት አስቸግሮኝ ስለ ነበር ብዙ ጨዋታዎችን አልተጫወትኩም። ተስፋ ቡድን ሆኜ ከአማካይ ስፍራ ከኋላ ተነስቶ ወደ ፊት በሚደረግ ሽግግር ውስጥ ጎል የማስቆጠር ጥሩ ነገር ነበረኝ። በዚህም ፈጥኜ ጎል ላይ በመድረስ በአጋጣሚ የሚገኙ ኳሶችን ወደ ጎልነት እቀይራለው ።

ጎል አስቆጥረህ ደስታህን የምትገልፅበት መንገገድ ለስፖርት ቤተሰቡ አዝናኝ እየሆነ መጥቷል። አስበህበት ነው ወይስ በአጋጣሚ ነው ?  

ያው ጎል አስቆጥረህ ደስታህን የምትገልፅበት የራስህ ቀለም ቢኖርህ ደስ ይላል። እኔ በዚህ አምናለው። እኔ ደግሞ የማንችስተር ዮናይትድ ተጨዋች የሆነው ፖል ፖግባ በጣም አድናቂ ነኝ። እሱ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ማድረግ ያስደስተኛል ። ጎል አስቆጥሬ ደስታዬን የምገልፀው ከእሱ አይቼ ነው ።

ከዳዋ ሆቴሳ ጋር የሚገርም ጥምረት እያሳያቹ ነው። ይህ ጥምረት መናበብ የመጣው ከምን አንፃር ነው። በቡድኑ ውስጥ ሁለታቹ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪም ናችሁ። እስቲ ግለፅልኝ  ?  

አዎ ጥሩ ቅንጅት አለን። ከሜዳም ውጪ ከዳዋ ጋር ጓደኛሞች ነን። በጣም ነው የምናወራው ፣ የምንግባባው። ወጣቶችም ስለሆንን እና ሜዳ ላይ ባለው ነገር አንድ ላይ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን በማድረጋችንም ነው አሁን ያለው ጥምረት እና ተግባብቶ የመጫወት ነገር መጥቷል ብዬ የማስበው።

ቀጣይ እቅድህ . . . 

ብዙ ነው የማስበው። ዋናው ግን በ2020 የኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የቻን ዋንጫ በቋሚነት ለመጫወት በጣም አስባለው። ለዚህም ከአሁኑ ጀምሬ ጠንክሬ እየሰራው እገኛለው። ከዚህ ባለፈ ከኢትዮዽያ ውጪ ወጥቶ መጫወት እፈልጋለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *