ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | ወላይታ ድቻ ከገነው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል

ወላይታ ድቻ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከዛንዚባሩ ዚማሞቶ ጋር በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም ያደርጋል። በዛሬው እለት ረፋድ ላይም የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

የአምናው የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ዛባንዚባር አቅንቶ ከዚማሞቶ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን ከጨዋታው መልስ ያለፉትን ስድስት ቀናት በሀዋሳ ፓራዳይዝ ሆቴል ማረፊያውን አድርጎ ልምምዱን አስቀድሞ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ከእሁድ ጀምሮ የመልሱ ጨዋታውን በሚያደርግበት የሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል። ነገ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊትም ዛሬ ረፋድ 4:20 አካባቢ ቀለል ያለ ልምምዱን ሰርቷል። በልምምዱም አካል ብቃት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንዲሁም የተሻጋሪ እና የመስመር ላይ ኳሶችን የተመለከተ ቀለል ያለ ልምምድን አድርገዋል። ክለቡ ወደ ዛንዚባር ሲያነቀና ይዟቸው የተጓዛቸውን 18 ተጫዋቾች በመያዝ ዝግጅቱን እያከነመወነ እንደሚገኝም ታውቋል።

ጨዋታው ነገ ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም የሚደረግ ሲሆን የጅቡቲ ዳኞች ጨዋታውን የሚመሩት ይሆናል። 1ኛ ደረጃ 100 ብር ፣ 2ኛ ደረጃ 50 ብር እና 3ኛ ደረጃ 30 ብር የስታድየም መግቢያ ዋጋዎቹ ናቸው።

ከወላይታ ድቻ ጋር በተያያዘ ዜና ከክለቡ እንደተሰናበተ ተገልፆ የነበረው ናይጄርያዊው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ በአሁኑ ሰአት በቡድኑ ውስጥ ባይገኝም በክለቡ እንደሚቆይ ስራ አስኪያጁ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *