​ፋሲል ከተማ ከሶስት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያየ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈፀሟቸው ዝውውሮች የሰመሩላቸው አይመስልም። ለአዳዲስ ተጫዋቾቻቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከመስጠት እስከ ቅጣት ብሎም ውል እስከማፍረስ እየደረሱ ይገኛሉ። ፋሲል ከተማም ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ከሶስቱ ጋር በስምምነት ውላቸውን ማቋረጡ ታውቋል።

አጼዎቹ በውድድር አመቱ መጀመርያ ወደ ቡድናቸው የቀላቀሏቸው ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ አቤል ውዱ እና ሮበርት ሴንቶንጎ ጋር ነው የተለያዩት። ዳዊት ኤሌክትሪክን ለቆ ወደ ፋሲል ካመራ በኋላ በጉዳት ምክንያት ጥቂት ጨዋታዎችን ብቻ አድርጎ በመጨረሻም ከክለቡ ጋር ተለያይቷል። ተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያው የቀድሞ ክለቡ ድሬዳዋ ከተማ እንደሚሆንም ተገምቷል። ዳዊት ወደ ፋሲል ከማቅናቱ በፊት ወደ ድሬዳዋ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ፊርማውን ሳያኖር ወደ ጎንደር ማቅናቱ የሚታወስ ነው።

ዩጋንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሴንቴንጎ ሌላው ከክለቡ ጋር የተለያየው ተጫዋች ነው። በክለቡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸው ከነበሩ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ሮበርት ከዚህ ቀደም ከክለቡ ተሰናብቶ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ቡድኑን ተቀላቅሎ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ከተጠባባቂ ወንበር ላይ በመነሳት ተጫውቷል። ሌላው ክለቡ አስጠንቅቆት የነበረው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አቤል ውዱ በውድድር አመቱ እምብዛም የመጫወት እድል አላገኘም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *