ቻምፒየንስ ሊግ | አብዱልከሪም ኒኪማ እና ቲሞቲ አዎኒ ስለነገው ጨዋታ ይናገራሉ

በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዩጋንዳውን ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶዎሪቲን ይገጥማል፡፡ ወደ ምድብ ለማምራት ወሳኝ ከሆነው ፍልሚያ አስቀድሞም የሁለቱ ክለብ ተጫዋቾች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“ወደ ምድብ እንደምናልፍ አምናለው” አብዱልከሪም ኒኪማ

ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅታዊ ደካማ አቋም

“አውቃለው ጨዋታዎችን ማሸነፍ በሚገባን መልኩ እያሸነፍን እንዳልሆነ ሆኖም ችግሮቻችን እና ድክመቶቻችን ለማረም እየጣርን ነው፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ወደ ምንፈልገው መልካም አቋም እንደምንመለስ ነው፡፡”

ስለተጋጣሚያቸው ኬሲሲኤ
“የተወሰኑ የጨዋታ ምስሎችን አይተናል፡፡ ምን አይነት ቡድን እንደሆኑ ለመረዳት በቂ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአእምሮም ሆነ በአካል ደረጃ ለኬሲሲኤ ተዘጋጅተናል፡፡ ለጨዋታው በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተናል፡፡”

ወደ ምድብ የማምራት እድል

“በአእምሮም በአካልም ጠንካራ ነን፡፡ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ እንምናመራ ተስፋ አደርጋለው፡፡ አላማችን ወደ ምድብ ከማለፍ በዘለለ ከዓምናው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነው ይህም ሲባል በቻምፒየንስ ሊጉ ርቆ መጓዝን ያጠቃልላል፡፡ ለዚህም ኬሲሲኤ ፈተና በድል መወጣት አለብን፡፡”

“ስለቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅታዊ ሁኔታ ማወቅ አይጠበቅብንም” የኬሲሲኤ አምበል ቲሞቲ አዎኒ

ስለኢትዮጵያ ቆይታ እና የአዲስ አበባ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳ
“ሜዳው መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡ ልምምዶችን እና ጨዋታዎችን በአብዛኛው ስናደርግ የነበረው የሰውሰራሽ ሳር የተነጠፈበት ሜዳ ላይ ስለነበር አሁን ላይ እዚህ ያለው የተፈጥሮ ሳር መሆኑ መልካም ይመስለኛል፡፡ የአየር ንብረቱም ዩጋንዳ ካለው ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ተፅእኖ የለውም ማለት እችላለው፡፡”

ስለተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸው መረጃ 

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ቡድን መሆኑን እናውቃለን፡፡ ከኳስ ጋር ጥሩ ናቸው፡፡ እኛም በተመሳሳይ ኳስን ይዘው መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች አሉን፡፡
“እውነት ለመናገር ስለእነሱ ጥልቅ የሆነ መረጃ ማወቅ አይጠበቅብንም፡፡ እራሳችን ለጨዋታው በበቂ ሆኔታ ማዘጋጀት ነው ያለብን፡፡”

ኬሲሲኤ ከሜዳው ውጪ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ስላለው መጥፎ ሪከርድ

“የነገው ጨዋታ ከዚህ በፊት ካደረግናቸው እና ከተሸነፍንባቸው የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ስህተቶቻችን ከጨዋታ ጨዋታ እያረምን ነው የሆድነው፡፡ ነገሮችን ወደ ጥሩ መንገድ እንዲጓዙ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ እኔ እንደማስበው ነገ ጥሩ የሆነ ጨዋታ እና ግጥሚያ እንደሚኖር ነው፡፡

“እኛ ያለን ብልጫ ከዓምና ጀምሮ በአህጉር ደረጃ ብዙ ጨዋታዎችን መጫወት መቻላችን ነው፡፡ ያሉን ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸው አድጓል፡፡ ቢሆንም በነገው ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *