​ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ዛማሌክን በመርታት ሀዋሳን በደስታ ማእበል ውስጥ አስጥሟታል 

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወላይታ ድቻ የግብፁ ዛማሌክን በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም 10፡00 ሰአት ላይ አስተናግዶ ከመልካም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ ከስታዲየሙ ውጭ ረጃጅም ሰልፎችን ያስተዋልን ሲሆን ዚማሞቶን በገጠመበት ጨዋታ ከገባው በእጅጉ የሚልቅ የተመልካች ቁጥር ተገኝቷል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም የጣለው ዝናብ አየሩን ተቀዛቅዞ የነበረው ድባብ በድንቅ የደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ደምቆ ውሏል። ወላይታ ድቻዎች ዚማሞቶን ከገጠመው ቡድናቸው ዳግም በቀለን በጉዳት በማጣታቸው ተስፉ ኤልያስ ተክቶት ሲገባ በተከላካዩ ሙባረክ ሽኩር ምትክ ውብሸት አለማየሁን አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በማሊያዊው ኢስማኤል ጄሲንጋ ዳኝነት የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪዎቹ 25 ደቂቃዎች ወላይታ ድቻ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ያስተዋልንበት የነበረ ቢሆንም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ዛማሌኮች ተሽለው ታይተዋል። በ4ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ፋቲህ የእሸቱ መናን የትኩረት ችግር ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ካሶንጎ ካቦንጎ ለጥቂት ሳይደርስባት በቀረው ኳስም የመጀመርያውን አጋጣሚ ፈጥረዋል። 


በተረጋጋ ሁኔታ በመቀባበል ወደ ዛማሌክ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ወላይታ ዲቻዎች በማጥቃት ወረዳው የነበራቸው ስኬታማነት ዝቅተኛ ነበር። ሆኖም በ16ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በኩል ያሬድ ዳዊት ወደ ሳጥኑ በመግባት ላይ ለነበረው በዜብህ መለዮ አሻግሮለት በዛብህ በማራኪ ሁኔታ በአህመድ ኤልሸነዊ መረብ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። የሀዋሳ ስታድየምም ወደር ወደሌለው የደስታ ድባብ ተቀይሯል።
ከጎሉ በኋላ ይበልጥ ተነቃቅተው መጫወት የቻሉት ድቻዎች ከጎሉ በፊት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ በተደጋጋሚ የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ዛማሌክን መፈተን ችለዋል። በተለይ 20ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት በጥሩ ሁኔታ የሰጠውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አብዱልሰመድ አሊ ሳይጠቀመምበት የቀረው አጋጣሚ የድቻን ልዩነት ልታሰፋ የምትችል ነበረች።


ጨዋታው 25 ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ ዛማሌኮች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም መግባት የቻሉ ሲሆን የአቻነት ጎል ለማስቆጠር የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በ36ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻው የመሀል ተከላካይ ተክሉ ታፈሰ ኳሷን ማራቅ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ቢገኝም ወደ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ሲመልስ ኳሷ በማጠሯ ከጀርባው የነበረው ኢማድ ፋቲህ ደርሶባት ወንድወሰንን በማለፍ ጭምር ግብ አስቆጥሮ ዛማሌክን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከዛማሌክ የአቻነት ጎል በኋላ በድቻ በኩል የጠሩ የግብ ሙከራዎች ባይታዩም ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃስሴን ያሳዩ ሲሆን በዛማሌክ በኩል በ41ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ሀዛም ኢማም በመስመር በኩል ሲያሻማ ካቦንጎ ካሶንጎ በግንባሩ ገጭቶ ኢላማዋን ሳትጠብቅ የወጣችው ኳስ እንዲሁም በድቻ በኩል ዘላለም እያሰለ ከያሬድ የተሻገረለትን ኳስ መትቶ በግቡ አናት ለጥቂት የወጣበት በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።


በሁለተኛ አጋማሽ ዛማሌኮች የአቻ ውጤቷን የፈለጉ በሚመስል መልኩ የጨዋታውን ፍጥነት ለማቀዝቀዝ ሲጥሩ ድቻዎች ደግሞ ጨዋታውን ለማሸነፍ በሙሉ ፍላጎት ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ደጋፊዎችን ለማነሳሳት ሲያደርግ የነበረው ጥረት አስገራሚ ነበር።
በ48ኛው ደቂቃ ተስፉ ኤልያስ ያሻገራትን ኳስ ጃኮ አራፋት በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ በወጣችበት ኳስ የዛማሌክን ግብ በሁለተኛው አጋማሽ መፈተሽ የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በተከላካይ መስመራቸው ላይ የሚሰሯቸው ስህተቶች በድጋሚ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ ነበር። በተለይ ተክሉ ታፈሰ በ56ኛው ደቂቃ ላይ የሰራው ስህተት ናይጄሪያዊው አማካይ ናሩፍ የሰስ አግኝቷት በሌላኛው ተከላካይ ውብሸት አለማየሁ ጥረት ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ አደገኛ ነበረች። 75ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሀምዛ ኢማም ወደ ውስጥ ሰብሮ ገብቶ ያሻማውን ኳስ መሀመድ አላህ በአክሮባቲክ ምት ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት ኳስም ዛማሌክን ወደ መሪነት ልታሸጋግር የተቃረበች ነበረች።


ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ድቻዎች ጫናቸውን አጠናክረው ቀጥለው በ77ኛው ደቂቃ በዛማሌክ ተከላካዮች የቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በዛብህ መለዮ በግሩም ሁኔታ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ያሬድ አሻግሮለት ወጣቱ ያሬድ በምርጥ አጨራረስ የድቻን ወሳኝ የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል። ከጎሉ በኋላም ኖኑ ቦኩ በግንባሩ ገጭቶ ወንደሰን ገረመው ከያዘበት ኳስ ውጭ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀዋሳ በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት  ደምቃ አምሽታለች። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *