ፋሲል ከተማ ዩጋንዳዊ አጥቂ አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተከታታይ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ የሚገኘው ፋሲል ከተማ የመጀመሪያውን ዙር ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ከሊጉ ክለቦች አምስተኛ በመሆን ነበር። ሆኖም ቡድኑ ካስመዘገባቸው 12 ግቦች መሀከል አብዘኞቹ በመሀል አጥቂ ስፍራ ተሰላፊዎች የተቆጠሩ አልነበሩም። ፊሊፕ ዳውዝ ፣ ራምኬል ሎክ እና መሀመድ ናስር እየተፈራረቁ የሚሰለፉበትን የፊት አጥቂ ቦታም ይበልጥ ለማጠናከር አፄዎቹ ሀሚስ ኪዛ የተባለውን ዩጋንዳዊ  ማስፈራማቸውን የክለቡ የፌስቡክ ገፅ በይፋ አስነብቧል።

ሀሚስ ኪዛ አምና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እስከ ሩብ ፍፃሜ ተጉዞ በቲፒ ማዜንቤ ተሸንፎ በወደቀው የሱዳኑ አል ሂላል ኦቢያድ አሳልፏል። ከዚያ አስቀድሞ በሀገሩ ክለብ ዩ.አር.ኤ ከ2006 እስከ 2011 ድረስ በመጫወት የቆየ ሲሆን በመቀጠልም በባላንጣዎቹ የታንዛንያ ክለቦች ያንግ አፍሪካ እና ሲምባ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካው ፊሪ ስቴስ ስታርስ ተጫውቶ አሳልፏል። ሀሚስ ኪዛ በ2010/11 የውድድር አመት በዩ.አር.ኤ ቆይታው ኮከብ ተጨዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን በቀጣዩም አመት በታንዛንያው ያንግ አፍሪካ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ክብር ደግሟል። ከዚህ በተጨማሪም ተጨዋቹ በ2012 ከያንግ አፍሪካ ጋር የሴካፋ ሻምፒዮን እና ኮከብ ግብ አግቢ የሆነ ሲሆን ለዩጋንዳ ቤሔራዊ ቡድንም በ26 ጨዋታዎች 11 ግቦችን አስቆጥሯል።

ሀሚስ ኪዛ ለፋሲል ከተማ  የፊት መስመር ጥያቄ መልስ ይሰጥ ይሆን ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *