​ባህርዳር ከተማ የምድቡ መሪ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል

የኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ተስተካካይ ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ቀጥለው ዛሬ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ 09:00 ላይ የካ ክፍለ ከተማን የገጠመው ባህርዳር ከተማ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 4-1 በመርታት የምድቡ መሪ መሆን ችሏል። 

በርከት ያለ የስፖርት ቤተሰብ በታደመመበት እንዲሁም በባህርዳር ከተማ ዳጋፊዎች ታጅቦ በተካሄደው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል በማስቆጠርም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ  ብልጫ የነበራቸው እንግዶቹ ባህርዳር ከተማዎች ነበሩ። በተለይ ወሰኑ አሊ በግል ጥረቱ ከግራ መስመር ጠርዝ እየተነሳ የሚፈጥረው የማጥቃት እንቅስቃሴ ለባህርዳር ብልጫ መውሰድ እና በርከት ያሉ የጎል እድሎች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆን ችሎ ነበር  ። የካ በአንፃሩ ጥሩ ኳስ የሚጫወቱ ተጨዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ቢሆንም በተጠና መልኩ ወደ ጎል የሚያደርገው ሽግግር ውስን በመሆኑ እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ አለመኖር ለተወሰደባቸው ብልጫ እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ነው። 

ባህርዳር ከተማ ጎል ማስቆጠር የጀመረው በ12ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ፍቅረሚካኤል አለሙ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት በግሩም ሁኔታ በመምታት ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ መሀል ሜዳውን  በሚገባ ተቆጣጥረው የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ባህርዳሮች በእንዳለ ከበደ ፣ በሳላምላክ ተገኝ እና ወሰኑ አሊ አማካኝነት ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። እረፍት ሊወጡ መዳረሻው 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተላከውን ኳስ ተቀይሮ እስከወጣበት ድረስ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ወሰኑ አሊ በግንባሩ በመግጨት የባህርዳር ከተማን ጎል ወደ ሁለት ከፍ አድርጎ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የካዎች ተጨማሪ ሦስተኛ ጎል እስካስተናገዱበት 65ኛው ደቂቃ ድረስ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጎልና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ባለመኖሩ ምክንያት ጎል ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ባህርዳሮች ደግሞ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾቹ አማካኝነት ታግዞ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ውስጥ እንዳለ ከበደ (በ65ኛው እና 67ኛው ደቂቃ) ባስቆጠራቸው ሁለት ግሩም ጎሎች አማካኝነት የግብ መጠናቸውን በማስፋት 4 – 0 መምራት ችለዋል። 

ባህርዳሮች በቀሩት 20 ደቂቃዎች ሌሎች ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት በመቅረታቸው እንጂ ከዚህ በላይ የጎል መጠናቸውን ማስፋት በቻሉ ነበር ። 84ኛው ደቂቃ ላይ አምና በመከላከያ ከ20 አመት በታች ቡድኑ ውስጥ በአምበልነት ይጫወት የነበረውና በዛሬው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ከገባ በኋላ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው በኃይሉ ኃ/ማርያም ለየካ የማስተሳዘያ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በባህርዳር ከተማ 4 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ በከፍተኛ ሁኔታ ደረጃውን ማሻሻል የቸመለው ባህርዳር ከተማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 25 ነጥቦች በመያዝ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *