ሲዳማ ቡና እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ይመራል

ከአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ጋር የተለያየው ሲዳማ ቡና በረዳት አሰልጣኝነት ሲሰራ የነበረው ዘርዓይ ሙሉን እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ በዋና አሰልጣኝነት እንዲቀጥል ወስኗል።

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ረዳት በመሆን ወደ ሲዳማ ቡና ከመጡ በኃላ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን ሲመሩ ቆይተው ባሳለፍነው ሳምንት ከክለቡ ጋር እንደተለያዩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ረዳት በመሆን ከ2009 ጀምሮ የሰራው የቀድሞው የክለቡ አምበል እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ዘርዓይ ሙሉም የአሰልጣኙን መሰናበት ተከትሎ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ሲዳማ ቡናን እየመራ እንደሚዘልቅ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘርዓይ ሙሉ በ2007 ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ራሱን ካገለለ በኋላ የሲዳማ ከ17 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ለአንድ አመት ካገለገለ በኋላ ነበር ወደ ዋናው ቡድን የተሸጋገረው። በቀጣይ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ምክትል ሆኖ የሚሰራው ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ የነበረው ካሳሁን ገብሬ መሆኑን ሰምተናል፡፡

ሹመቱን ተከትሎ አሰልጣኝ ዘርዓይ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በሹመቱ እንደተደሰተ ተናግሯል፡፡ ” እድሉን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ለስራው አዲስ ብሆንም ባለኝ የተጫዋችነት እና የትንሽ ጊዜ የአሰልጣኝነት ቆይታዬ ያገኘሁትን ልምድ በአግባቡ ተጠቅሜ ክለቡን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እጥራለው።” ሲል ሀሳቡን ሰንዝሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *