አሳልፈው መኮንን ወደ ወልዲያ አምርቷል

በጉዳት እና በሌሎች ምክንያቶች በርከት ያሉ ተጨዋቾቹን አገልግሎት በሚገባ ማግኘት ያልቻለው ወልዲያ ወደ ዝውውር ገበያው እንደሚወጣ ሲጠበቅ ነበር። በዚህም መሰረት ክለቡ የቀድሞውን የኢትዮ ኤሌክትሪክ የተከላካይ እና የአማካይ ቦታ ተሰላፊ የነበረውን የመስመር ተጨዋች አሳልፈው መኮንንን ማስፈረሙ ታውቋል።

አሳልፈው መኮንን አምና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ለረጅም ወራት በጉዳት ከሜዳ ርቆ የቆየ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር አመት ደግሞ ወላይታ ድቻን መቀላቀሉ የሚታወስ ነው። ተጨዋቹ በሶዶው ክለብ ባደረገው የስድስት ወር ቆይታ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ብቻ የመሰለፍ ዕድል ያገኘ ሲሆን አሁን ደግሞ በአንድ አመት ከስድስት ወር ውል ወልዲያን ተቀላቅሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ወልዲያ ለሁለት የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች የሙከራ ጊዜ ዕድል መስጠቱ ተሰምቷል። ተጨዋቾቹ አምና በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ ያደረገው አልሳዲቅ አልማሂ እና በአመቱ መጀመሪያ በአዲስ አበባ ዋንጫ በኢትዮ ኤሌክትሪክ መለያ የተመለከትነው የድሬደዋ ከተማው በላይ አባይነህ እንደሆኑ ታውቋል። ሁለቱ ተጨዋቾች የሙከራ ጊዜውን በስኬት ካጠናቀቁ ቀጣዮቹ የወልዲያ ፈራሚዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *