ቻምፒየንስ ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ካምፓላ አምርቷል

በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ለመግባት የሚደረጉ ጨዋታዎች ከአርብ ጀምሮ ሲደረጉ በውድድሩ ላይ ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ ወደ ምድብ ለማለፍ አላማውን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዩጋንዳው ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ኬሲሲኤ) ጋር ለሚያደርገው ወሳኝ ፍልሚያ ወደ ካምፓላ ዛሬ ረፋድ አምርቷል፡፡

የፈረሰኞቹ ልኡካን በእንቴቤ የአየር ማረፊያ ሲደርሱ የዩጋንዳ እግርኳስ ፌድሬሽኖች ማህበር (ፉፋ) እና የኬሲሲኤ ክለብ ሃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ግጥሚያ ያለግብ ጨዋታዎችን ያጠናቀቁ ሲሆን ሉጎጎ በሚገኘው ስታር ታይምስ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ ባለሜዳው ኬሲሲኤ ከ2017 ጀምሮ በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ሽንፈትን ባለመቅመሱ ወደ ምድብ የማለፍ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው አስችሏል፡፡ ፖርቹጋላዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ካርሎስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ካስቸጋሪው ጨዋታ ውጤትን ይዞ ለመመለስ ዋነኛ እቅዱ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡

“በዚኛው ጨዋታ ሁሉም ነገር ክፍት ነው፡፡ አሁን ላይ ለእኛ ጥሩ የሚባሉ ምሳሌዎች በእግርኳሱ ዓለም በቅርብ ቀናት ተከስተዋል፡፡ ለምሳሌ ዩቬንቱስ በሜዳው 2-2 ተለያይቶ እንግሊዝ ሄዶ ቶትነሃምን ያሸነፈበት እና ሲቪያም በተመሳሳይ በሜዳው አቻ ቢለያይም ከሜዳው ውጪ ማንቸስተር ዩናይትድን አሸንፏል፡፡ እኚህ ለእና ጥሩ ትምህርት የሚሆኑን ትምርቶች ናቸው፡፡ ዋናው ቁምነገር እኛ ያለን የትኩረት ደረጃ ነው፡፡ ተጫዋቾቻችን እና ሁሉም የቡድኑ አባላት ወደ ቀጣይ ዙር እንደምናልፍ ያምናሉ፡፡ ጨዋታው አስቸጋሪ እንደሆነ እናውቃለን ምክንያቱም ኬሲሲኤ በሜዳው በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ዝግጅታችን ጠንካራ ነበር፡፡ በተለይም በአእምሮ ደረጃ የነበረን ዝግጅት ጥሩ የሚባል ስለሆነ በካምፓላ ጥሩ ጨዋታ እንደምናሳይ ተስፋ አለኝ፡፡”

ቫዝ ፒንቶ ፈረሰኞቹን ከያዙ አንስቶ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚያምን ቡድን ለመገንባት እየሞከሩ እንደሆነ ቢታይም በፍልስፍናቸው ይህንን ብቻ ለመተግበር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳልመጡ ይናገራሉ፡፡

“አንድ የተሳሳተ ሃሳብ አለ በእኔ ቡድን ላይ፡፡ በ2 ቅብብሎች ግብ ማስቆጠር ከቻልን 20 ቅብብሎችን ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ በሁለት ሰከንድ ግብ ማስቆጠር ከቻልን 20 ሰከንድ ለማስቆጠር መጠበቅ የለብንም፡፡ የእኛ ሃሳብ ቡድናችን ሁሌም ጨዋታውን እንዲቆጣጠር እና እንዲመራ ነው፡፡ ይህ የተለየ ሃሳብ ነው፡፡ ሆኖም ካምፓላ ላይ የተወሰኑ ነገሮችን የምንለውጥ ይሆናል ምክንያቱም ሜዳው እና የምንገጥመው ቡድን የተለዩ ናቸው፡፡ ሁሌም በተጋጣሚያችን አጨዋወት ላይ ተመስርተን ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ካምፓላ ስንሄድም ኳስ ለመቆጣጠር ነው የምንሄደው ለማሸነፍ ስለምንፈልግ መከላከልን ብቻ አቅደን አንገባም፡፡”

ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት አጥቂው ሳላዲን ሰዒድ ጉዳቱ ያገረሸበት በመሆኑ ከጨዋታው ውጪ ነው፡፡ ኮትዲቯራዊው ኢብራሂማ ፎፋና እና ማሊያው አጥቂ ኬታ ሴዲ ከጨዋታው ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ፈረሰኞቹ ዛሬ ካምፓላ ላይ የመጀመሪያ ልምምዳ መሰራታቸው የክለብ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ጠቁሟል፡፡ ኬሲሲኤ በመጪው ቅዳሜ ቅዱስ ጊዮርጊስ በስታር ታይምስ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ሮበርት ኦዶንካራ፣ ለዓለም ብርሃኑ

ተከላካዮች፡

አስቻለው ታመነ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ አብዱልከሪም መሃመድ፣ አበባው ቡታቆ፣ ደጉ ደበበ፣ መሃሪ መና፣ ፍሬዘር ካሳ

አማካዮች፡

ሙሉአለም መስፍን፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ፣ ታደለ መንገሻ፣ አዳነ ግርማ

አጥቂዎች፡

ጋዲሳ መብራቴ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ አሜ መሃመድ፣ አማራ ማሌ፣ አቡበከር ሳኒ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *