ወልዲያ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ወልዲያ እንደ ክረምቱ ሁሉ አሁንም በዝውውር ሂደቱ ላይ በስፋት በመሳተፍ አንድ ተከላካይ እና አንድ አማካይ ማስፈረም ችሏል።

የአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊሱ ወልዲያ ዛሬ የሁለተኛው ዙር ሶስተኛ ተጨዋቹን አስፈርሟል፡፡ በሊጉ በበርካታ ችግሮች ውስጥ አልፎ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው ወልዲያ አስቀድሞ በቀጣቸው ተጫዋቾች ፍፁም ገ/ማርያም ታደለ ምህረቴ እና ያሬድ ብርሀኑ ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እያመጣ ይገኛል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አዳማ ከተማን ለቆ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው የመሀል ተከላካዩ ሞገስ ታደሰ በአንድ አመት ከስድስት ወራት የውል ኮንትራት ነው ወደ ወልዲያ ያመራው። ሞገስ በቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ጅማሮውን በማድረግ ወደ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ሄዶ ከተጫወተ በኃላ ነበር የኢትዮ ኤሌክትሪኩን ዝውውር የፈፀመው። ሆኖም በክለቡ ባሳየው ደካማ የውድድር አመት ምክንያት ቀሪ የውል ኮንትራቱን ሳይጨርስ ወደ አዲሱ ክለቡ አቅንቷል፡፡ ሌላኛው ፈራሚ መስፍን ኪዳኔ ነው። የቀድምው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሀል ሜዳ ተጨዋች በተመሳሳይ መከላከያን ለቆ ወልዲያ ከተማን በአንድ አመት ከስድስት ወራት ኮንትራት የተቀላቀለ ተጨዋች ሆኗል።

ወልዲያ ተከላካዩ አሳልፈው መኮንንን ከወላይታ ዲቻ አስቀድሞ ያስፈረመ ሲሆን አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ክለቡ በሁለተኛው ዙር የተሻለ ሆኖ እንዲቀርብ አሁንም በክፍት ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ተጨዋቾች ለማምጣት እንዳሰበ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *