ፍቅሩ ተፈራ ዳግም ወደ ህንድ አምርቷል

በኢትዮጵያ ተጫዋቾች ታሪክ ለረጅም ግዜያት በውጭ ሃገራት ሊጎች በመጫወት በተለይም በቅርብ አመታት ውስጥ የሚስተካከለው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች የለም፡፡ የፊት አጥቂው ፍቅሩ ተፈራ ከረጅም ወራት ቆይታ በኃላ ወደ እግርኳስ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ ፍቅሩ ለህንዱ አይ ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ መሃመዳን ስፖርቲንግ ክለብ ለመጫወት ተስሟምቷል፡፡ መሃመዳን ለፍቅሩ 16ኛው ክለቡ ነው፡፡

በራሪው ፍቅሩ በሚል ተቀፅላ ስም በህንድ የተሰጠው ተጫዋቹ አምና በደቡብ አፍሪካ ሃይላንድስ ፓርክ ቆይታ ያደረገ ሲሆን በቀጣይ ማረፊያው ህንድ ሊሆን እንደሚችል በስፋት ሲነገር ቆይቷል፡፡ ፍቅሩ በህንድ ሂሮ ሊግ ለሚወዳደረው የቀድሞ ክለቡ አትሌቲኮ ኮልካታ ለመመለስ ያልተሳካ ድርድር አድርጓል፡፡እንደኢስት ቤንጋል እና ሞሃን ባጋን ያሉ ክለቦችም ፍቅሩን ለማስፈረም ጥረት ያደረጉ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ከሶስት ወራት ወዲህም ከተለያዩ የህንድ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቶ ለመሃመዳን እስከዓመቱ መጨረሻ ለመጫወት ተስማምቷል፡፡ ክለቡንም ዛሬ በይፋ ተቀላቅሏል፡፡ ሆኖም ቅዳሜ በሚደረግ የሊግ ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፍ ክለቡ አሳታውቋል፡፡

ፍቅሩ በመሃመዳን የቴሬናዳድ እና ቶባጎ ተወላጁን ዊሊስ ፕላዛ ከክለቡ መለያየቱን ተከትሎ የተፈጠረው ክፍተት እንደሚሞላ ይጠበቃል፡፡ መቀመጫውን በኮልካታ ያደረገው መሃመዳን ለፍቅሩ ሶስተኛው የህንድ ክለቡ ነው፡፡ ከዚህ አስደቀድሞ ለአትሌቲኮ ኮልካታ እና ቼናይ ፍቅሩ መጫወት ችሏል፡፡ በሁለቱም ክለብ ቆይታም የሊግ ድሎችን ማጣጣም ችሏል፡፡ ፍቅሩ እግርኳስን በሃገሩ ኢትዮጵያ ለአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፊንላንድ፣ ቬይትናም፣ ፣ ህንድ እና ባንግላዴሽ መጫወት የቻለ አንጋፋ አጥቂ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *