ሽመልስ በቀለ ለወላይታ ድቻ በሆቴል በመገኘት የማነቃቂያ መልዕክት አስተላለፈ 

ወላይታ ድቻዎች ዛሬ ማምሻውን ከግብፁ ዛማሌክ ጋር ላለባቸው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ የቡድኑ አባላት ወደ ካይሮ ካቀኑበት ጊዜ ጀምሮ በካይሮ ለጨዋታው የሚረዳቸውን በቂ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ በመስራት የዛሬውን ጨዋታ መካሄድን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ኢትዮዽያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ክለቡ ፔትሮጀት በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ከኢትሀድ አሌሳንድርያ ጋር ነገ ማምሻውን ጨዋታ የሚያደርግ በመሆኑ ዛሬ ወደ አሌክሳድርያ ከተማ ይጓዛል። ይህ በመሆኑ የዛሬውን የወላይታ ድቻን ጨዋታ በስታድየም ተገኝቶ የመመልከት አጋጣሚ አይኖረውም። ሆኖም ሽመልስ የወላይታ ድቻ ቡድን አባላት ያረፉበት ኖቫ ሆቴል ድረስ በመሄድ ከልምዱ በመነሳት የዛሬውን ጨዋታ አስመልክቶ የማነቃቂያ መልዕክት አስተላልፏል።

“ምንም አይነት ፍራቻ በውስጣችሁ መኖር የለበትም። ሁሉንም ነገር ማድረግ የምትችሉበት አቅም አላችሁ ፤ በደንብ ማሸነፍ ትችላላቹሁ። ስህተት በምንም መንገድ እንዳትሰሩ ጥንቃቄ አድርጉ። የመስመር ላይ ኳሶችን መጠንቀቅ አለባቹሁ። የቆሙ ኳሶች እንዲያገኙ መፍቀድ የለባችሁም። የራሳችሁን ጨዋታ እየተጫወችሁ እና በቡድኑ ላይ ጫና በማሳደር ከተጫወታችሁ ማሸነፍ ትችላላችሁ። ዛማሌኮች ጫና የሚፈጥሩት እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ ነው ከዚህ በኋላ እየደከሙ ነው የሚመጡት። ጨዋታውን ባይ ደስ ይለኝ ነበር ስራ በመሆኑ የማየት እድሉን አላገኘሁም። በርቱ!” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።
በመጨረሻም የክለቡ አመራሮች ለሰጣቸው ምክራዊ ድጋፍ አመስግነው በህብረት ሆነው ፎቶ ከተነሱ በኋላ ተለያይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *