ከፍተኛ ሊግ | ባህርዳር ከተማ በግስጋሴው ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ አንድ የ14ኛ ሳምንት እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ተደርገው አናት ላይ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ እና ግርጌ ላይ የተቀመጠው ነቀምት ከተማ አሸናፊ ሆነዋል።

በባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ባህርዳር ከተማ በምድብ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሰበታ ከተማን አስተናግዶ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል አሸንፎ ወጥቷል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች በሜዳቸው የሚያደርጉት የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ እንደመሆናቸው ለአሰልጣኝ ጳውሎስ እና ረዳታቸው መኮንን በስማቸው የታተመ የቡድኑን መለያ በቡድኑ አምበል ደረጄ መንግስቱ አማካኝነት በስጦታ መልክ ሲያበረክቱ አሰልጣኞቹም ስታዲየሙን በመዞር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለት የተለያየ መልክ የነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብዙም ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያልተስተዋለ ሲሆን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ሲበላሹ ተስተውሏል። ባለሜዳዎቹ ባህርዳሮች በመጀመሪያው አጋማሽ የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት ማስከፈት አቅቷቸው ሲቸገሩ ተጋባዦቹ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ተከላክለው ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ባህርዳር ከተማዎች በ12ኛው ደቂቃ በፍቅረሚካኤል አለሙ አማካኝነት ያገኙ ሲሆን ከደረጄ መንግስቱ የተሻገረውን ኳስ ፍቅረሚካኤል በግምባሩ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። በዛሬው ጨዋታ የባህርዳር ከተማ ዋነኛ የማጥቃት ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ግርማ ዲሳሳ በግሉ በርከት ያሉ ኳሶችን ሲሞክር እንደነበረ የታየ ሲሆን በ22 ደቂቃ ለእንዳለ ከበደ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው እንዳለ ሳይጠቀምበት ኳሷ ወደ ውጪ ወጣች እንጂ ገና በጊዜ ባለሜዳዎቹ መሪ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በተመሳሳይ ግርማ ከመስመር ተነስቶ የሰበታ ተከላካዮችን በመሸወድ ወደ መሃል በመግባት የሞከረውና የግቡን መረብ ታካ ወደ ውጪ የወጣችው ሙከራ ባህርዳሮችን በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ልታደርግ የምትችል ሌላኛዋ አጋጣሚ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ በትንሹም ቢሆን ተጠናክረው የገቡት ተጋባዦቹ በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም እና ኳሶችን በረጃጅሙ ወደ አጥቂዎቻቸው በመላክ ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ብዙም ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተቃራኒው ባህርዳር ከተማዎች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ለማሸነፍ የተጨዋቾችን ለውጥ ጨምሮ የፎርሜሽን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ተደጋጋሚ ጫናዎችን ተጋጣሚያቸው ላይ ሲያሳድሩ ታይቷል።

በ56ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ታሪኩ ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አሰግድ አክሊሉ ወደ ውጪ ያወጣው ሲያወጣበት ያንኑ ኳስ ከማዕዘን ሲሻማ ራሱ ሙሉቀን አግኝቶት በግምባሩ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የተገኘ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። በሙከራዋ የሰበታ ከተማ ተጨዋቾች ያሳዩት የመዘናጋት ስህተትም ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ ነበር።

ሰበታ ከተማዎች በጨዋታው ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ያገኙት በ65ኛው ደቂቃ ሲሆን ዳንኤል ታደሰ በረጅሙ የተመታለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ለአብይ ቡልቲ አቀብሎት አብይ ኳሷን ሞክሯት በአስገራሚ ሁኔታ ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ አምክኖበታል። የጨዋታው ማገባደጃ ላይ ባለሜዳዎቹ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው በፍቃዱ ወርቁ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገው በመጨረሻም በ89ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ደጋፊዎችን ጮቤ አስረግጧል። 

ከጎሉ መቆጠር በኋላ የመጨረሻው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የባህርዳሩ ሐብታሙ ንጉሴ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ሁለት ቢጫ በማየቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በባህርዳር 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአንደኛ ሳምንት ሳይደረግ በተስተካካይ መርሀ ግብር ተይዞ የነበረውና ውጤቱ ለሁለቱ በወራጅ ቀጠና ለሚገኙ ቡድኖች ወሳኝ የነበረው የነቀምት ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ጨዋታ ዛሬ ተካሂዶ ባለሜዳው ነቀምት ከተማ 2-1 አሸንፏል። እንግዶቹ ኮምቦልቻዎች በኄኖክ ነጋሽ የ5ኛ ደቂቃ ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ደረጄ ነጋሽ ነቀምትን አቻ ማድረግ ችሏል። በ85ኛው ደቂቃ ደግሞ ገዛኸኝ ባልጉዳ ወሳኟን የነቀምት የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *