ጋና 2018 | ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል

በ2018 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ሉሲዎቹ  ከሊቢያ ጋር ላለባቸው የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እየተመሩ ከየካቲት 28 ጀምሮ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። 

አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የመጨረሻ 25 ተጫዋቾችን ከያዘችበት መጋቢት 4  ጀምሮ ቡድኑ ሙሉ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ምንም እንኳን ከአቻ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ባያደርጉም ከታዳጊ ወንዶች ጋር ሁለት ጊዜ ጨዋታ በማድረግ የቡድኑን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ለማየት ተሞክሯል። ነገ 09:00 ላይም በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ከታዳጊ ወንዶች ቡድን ጋር የመጨረሻ የአቋም መፈተሻ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ለማወቅ ችለናል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ የ25 ተጫዋቾች ስብስብ ውስጥ ተካታ የነበረችው የደደቢቷ አማካይ ብሩክታዊት ግርማ እግሯ ላይ ባጋጠማት ጉዳት ምክንያት ከሉሲዎቹ ስብስብ ውጭ ስትሆን እርሷን በመተካት የደደቢቷ አንጋፋ አማካይ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ተጠርታ ዛሬ ልምምድ ጀምራለች።
ሶከር ኢትዮዽያ ሉሲዎችን የዛሬ ውሎ ልምምድ ለመቃኘት ወደ ስፍራው ባቀናችበት አጋጣሚ ያለፉትን 15 ቀናት ልምምድ ሲሰሩበት የነበረው የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ” ከላይ የተላለፈ ትዕዛዝ ነው ” በሚል የአካዳሚው የጥበቃ ሰራተኞች ሉሲዎችን የያዘው መኪና ወደ ግቢው እንዳይገባ መከልከላቸውን ተመልክታለች። የቡድኑ አባላት ለ15 ደቂቃ ያህል ሳይገቡ የቆዩ ሲሆን አሰልጣኞቹ ቢሮ በመሄድ አስፈቅደው እንዲገቡ ተደርጓል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከሊቢያ ጋር ለሚኖረው የመጀመርያ ጨዋታ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ 18 ተጫዋቾችን ይዛ እሁድ ማምሻውን ወደ ካይሮ የምታቀና ሲሆን ከቡድኑ ጋር አብረው የማይጓዙት 7 ተጨዋቾችን የፊታችን ቅዳሜ  ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታውም መጋቢት 26 ዕለተ ረቡዕ 10:00 ላይ የሚደረግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *