ከ17 እና 20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ግምገማ ተካሂዷል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከሚያዘጋጃቸው የታዳጊ እና ወጣቶች ውድድሮች መካከል የሆኑት ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊጎች የውድድር አጋማሽ ግምገማ አርብ በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል፡፡ ግምገማው በባለፉት ሳምንታት ከተደረጉት ግምገማዎች የተለየ መልክ አልነበረውም፡፡

ግምገማውን ያስጀመሩት የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት ጁኒይዲ ባሻ በመክፈቻ ንግግራቸው ክለቦች በታዳጊዎች እና ሴቶች እግርኳስ ላይ የሚሰጡትን ትኩረት እንዲያሻሽሉ አሳስበው ሀዋሳ ከተማ በወጣቶች ላይ እየሰራ የሚገኘውን ስራ አድንቀዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ጨምረው የእድሜ ተገቢነት ላይ ያሉ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ የሚደረጉ ስራዎችን እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ዶክተር አያሌው ጥላሁን ሰፋ ያለ ግዜ ወስደው በእድሜ ተገቢነት እና ምርመራ ላይ የተሰሩ ስራዎችን አቅርበዋል፡፡ እንደዶክተር አያሌው ገለፃ ከሆነ ወደ 74 የሚጠቁ ታዳጊዎች በፕሪምየር ሊግ እና በተለያዩ ሊጎች በሚሳተፉ ክለቦች ዋና ቡድን ላይ መጠቃለል የቻሉ ሲሆን ከዚህም ባለፈ የእድሜ ተገቢነት ላይ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ከዓመት ዓመት መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በግምገማው የተሳተፉ ክለቦች በበኩላቸው የውድድር አጋማሹ ችግሮች ናቸው ያሏቸውን አቅርበዋል፡፡

– ሚዲያዎች ለታዳጊ ውድድሮች በቂ የሆነ ትኩረት አለመስጠት

– ለጨዋታዎች የተጋጣሚ ቡድኖች አርፍዶ መምጣት

– የመወዳደሪ ስፍራዎች ጥራት

– ጨዋታዎች በአመቺ ሰዓት ያለመካሄድ

– በግምገማው የቴክኒክ ሪፖርት አለመቅረብ

– ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር እንዲሁም ከ17 ዓመት በታች ምክትል አሰልጣኝ ሹመት

– የዳኝነት ችግሮች

– የኤምአርአይ ምርመራ ተገቢነት

– ኮሚኒኬ በፍጥነት ያለመድረስ

– የጨዋታዎች ማነስ

የተጠቀሱት ችገሮችን ለማረም ፌድሬሽኑ እንደሚሰራ ጠቁሞ በተለይም ከመወዳደሪ ስፍራዎች ጋር የተያያዘውን ችግር ክለቦችን የራሳቸውን መፍትሄ እንዲወስዱ አስገንዝቧል፡፡ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ውድድሮችን በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ውሳኔ እንደሚደረስም ተነግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *