ኒጀር 2019 | ኢትዮጵያ በሜዳዋ በቡሩንዲ ተሸንፋለች

ኒጀር በሚቀጥለው ዓመት ለምታዘጋጀው የቶታል የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ቡሩንዲን ያስናገደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓት በታች ብሄራዊ ቡድን 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ እንግዶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ንጎዚ ላይ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ አስተማማኝ ውጤትን ማግኘት ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡድን ጨዋታው ጅማሮ ላይ በቡሩንዲዎች ጥቃት መጋለጡ እና ግብ ማስተናገዱን ተከትሎ ለረጅም ደቂቃዎች ከተጋጣሚ በተሻለ የግብ እድሎችን እንዲፈጥር አስችለውታል፡፡ ሆኖም በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ከመሃል ተከላካዮቹ ለጫላ ተሺታ እና አቡበከር ነስሮ ይላኩ የነበሩ ኳሶችን እምብዛም ስኬታማ አልነበሩም፡፡

ቡሩንዲዎች ጁማ መሃመድ ከ16.50 ውጪ ቀጥታ መቶ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከመሪነት ግቡም በኃላ በሚገኙ እድሎች እንግዶቹ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ እዮብ አለማየሁ ከደቂቃዎች በኃላ ከማዕዘን ምት በአጭር ቅብብል የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በግሩም ሁኔታ ቢመታም የቡሩንዲ ግብ ጠባቂ ሉኩንዶ ኦንሲሜ አምክኖበታል፡፡ በ22ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን እና ግብ ጠባቂው ፅዮን መርድ ከግብ ክልሉ ያላራቀውን ኳስ ተጠቅሞ ሻካ ቢቴንዩኒ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውጤቱን ለማጥበብ እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ስታደርግ የተገኙት ግቦች የቡሩንዲን በራስ መተማመን እንዲያድግ ያስቻለች ነበረች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በረጅሙ የሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጀመሪው አጋማሽ መጠናቀቂ ድረስ ቢጠቀምም ይህ ነው የሚባል የግ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በአንድ አጋጣሚ እዮብ ከመስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደ በሳጥኑ ውስጥ ለጫላ ለማቀበል ቢሞክርም የቡሩንዲ ተከላካዮች ኳስን አርቀዋል፡፡

በሁለተኛው 45 የሚኪያስ መኮንን ወደ ሜዳ ተቀይሮ መግባትን ተከትሎ ቡድኑ ተጋጣሚው ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ወስዷል፡፡ ቡሩንዲዎች ወደ መከላከሉ ሲያመዝኑ በብቸኛ አጥቂነት ለተሰለፈው ሻካ የኢትዮጵያ የተከላካይ መስመር ላይ አልፎ አልፎ ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አጨዋወት ወደ 4-3-3 የተጠጋ መመሰሉ እና የተከላካይ ክፍሉ ወደ መሃል ሜዳው መጠናጉትን ተከትሎ ቡሩንዲዎች በመከላካሉ እንዲጠመዱ ቢደርጋቸውም ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን እድል ሻካ አግኝቶ አጠገቡ ለነበረው መሃመድ ቢቀብልም በማይታመን መልኩ እድሉን አበላሽተዋል፡፡ የሚኪያስ ወደ ሜዳ መግባት ባለሜዳዎቹ በተሻለ ቅብብሎችን እንዲያደርጉ ቢያስችልም ወደ ሳጥኑ ውስጥ በሚደረግ ሽግግር ኳሶች በቀላሉ የቡሩንዲ ተከላካዮች ሲሳይ ይሆኑ ነበር፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ሚኪያስ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ በግብ አናት ሲወጣ በአቡበከር ከርቀት የሞከረውን ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

ቡሩንዲ ከሶስት ሳምንት በኃላ ንጎዚ ላይ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ከኢትዮጵያ የተሻለ ውጤትን አስመዝግባለች፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ዙር ለማለፍ በብሩንዲ ሜዳ ከሁለት በላይ ግቦችን አስቆጥሮ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብታለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *