ሀዋሳ ከተማ በወልዲያው ጨዋታ ዙርያ ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አቅርቧል

ሀዋሳ ከተማ በሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስታድየም ከወልዲያ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ላይ በደል ደርሶብኛል በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ አቤቱታውን አሰምቷል። በጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ 48ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ባስቆጠራት ግብ ሀዋሳ ከተማ መሪ መሆን ቢችሉም በመጨረሻው ደቂቃ ጭማሪ ሰአት ላይ ወልዲያ በምንያህል ተሾመ አማካኝነት ግብ አስቆጥሮ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂዎችም ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ታይተዋል።

በጨዋታው ላይ በርካታ በደሎች ደርሰውብኛል በማለት የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ በእለቱ ዳኛ እና በወልዲያ ላይ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው ደብዳቤ ገልጿል። ” በእለቱ የወልዲያ ተጫዋቾች በተጫዋቾቻችን ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫናዎች አድርሰዋል ፣ በሜዳ ላይም አላስፈላጊ ድርጊቶችን ሲፈፅሙብን ነበር። ወደ ወልዲያ የተጓዙት የደጋፊ ማህበር አመራሮች እንግልት ፈፅመውባቸዋል ፣ የክለባችን የካሜራ ባለሙያ የቀረፀውን ምስል እንዲደመስስ በማድረግ የመቅረጫ ሌንሱን ወስደውብናል።” የሚል ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ጨዋታውን በመራው ፌዴራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ ጨዋታውን በአግባቡ መምራት እንዳልቻለ እና በሜዳ ላይ በተጫዋቾች የሚደረጉ አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶችንም በዝምታ እንዳለፈ በደብዳቤው ገልጿል።

በተጨማሪነትም የክለቡ ቴክኒካል ዳይሬክተር እና የክለቡ ቡድን መሪ አቶ አለምአንተ ማሞ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ “እኛ ውጤት ይቀየርልን ብለን አይደለም ቅሬታችንን ያቀረብነው። ውጤትም ሊቀየር አይችልም ፤ የእለቱ የጨዋታ ኮሚሽነር በሚፅፈው ሪፖርት ላይ ለማጠናከር አስበን ነው። ይህም የደረሰብንን ለፌዴሬሽኑ ማሳወቅ ስላለብንን ጭምር ስለሆነ ፌድሬሽኑ ይሄን አይቶ እና ቅሬታችንን ተቀብሎ ውሳኔ እንዲሰጥልን ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *